የተጀመረው የመደመር ጉዞ ቀጣይነት እንዲኖረው የኅብረተሰቡ ድጋፍ እንዲቀጥል ተጠየቀ

የተጀመረው የይቅር ባይነት፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የመደመር ጉዞ ቀጣይነት እንዲኖረው ኅብረተሰቡ እስካሁን ያደርግ የነበረውን ድጋፍና ትብብር አጠናክሮ  እንዲቀጥል  መንግሥት ጥሪ አቀረበ።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ መንግሥት ነባራዊ የኢትዮጵያን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት እየሰራ ነው።

ሕጉን ለሁሉም ኃይሎች እኩል ለማድረግ ቀን ከሌት በመታተር ላይ እንደሆነ ያመለከተው መግለጫው ”ይህ የመንግሥት ቀና አካሄድ ለአንዳንድ ኃይሎችና ግለሰቦች ምቾት አልሠጠም” ብሏል።

በእንዲህ ያለ ኋላ ቀር የፖለቲካ አካሄድና አስተሳሰብ የተዘፈቁ ኃይሎች ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት ከሚያደርጓቸው ሴራዎች ባሻገር ህዝቦች በለውጥ ሂደቱ ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው እየሠሩ መሆናቸውን ጠቁሟል።

መንግሥት እየተፈፀሙ ያሉ የፖለቲካ ደባዎችን በሆደ ሰፊነት ማለፍን የመረጠው አገራዊ  መግባባትንና አንድነትን ለማጎልበት ካለው ጽኑ አቋም እንጂ እየተፈፀሙ የፖለቲካ ቅሌቶች ተጠያቂነትን የማያስከትሉ ሳይሆኑ ቀርተው እንዳልሆነ አመልክቷል።

መንግሥት የጀመረውን የዴሞክራሲ ምህዳሩን የማስፋት ሂደት አጠናክሮ ከመቀጠል ጎን ለጎን በእንዲህ ዓይነት እኩይ ተግባር ውስጥ የተዘፈቁ  ሃይሎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ   አሳስቧል።

የተጀመረው የይቅር ባይነት፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የመደመር ጉዞ  ቀጣይነት እንዲኖረው ኅብረተሰቡ እስካሁን ያደርግ  የነበረውን  ድጋፍና ትብብር አጠናክሮ  እንዲቀጥል  መንግሥት ጥሪውን  አቅርቧል።(ኢዜአ)

የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት መግለጫ  እንደሚከተለው ቀርቧል

 

በኢፌዴሪ  የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት

ሳምንታዊ የመንግሥት አቋም መግለጫ

 

የፖለቲካ ምህዳሩን  በማስፋት  የዴሞክራሲ ሥርዓቱን  ይበልጥ እናጎለብታለን!

መንግሥት የህዝቦችን  የለውጥ ፍላጎት  ለማርካት  እያካሄዳቸው  ካሉ  በርካታ  ተግባራት መካከል የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ለሁሉም እኩል  የማድረግ ተግባር  ቀዳሚው ነው። ኢትዮጵያ ከሦስት ወራት በፊት  እጅግ አስፈሪ ወደነበረ  ግጭትና ያለመረጋጋት አምርታ የነበረው  በፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ ሳቢያ  የዴሞክራሲ ሥርዓቱ አጣብቂኝ ውስጥ በመውደቁ ነበር።  ባለፉት ጥቂት ጊዜያት ውስጥ መንግሥት አገራዊ መግባባትን ለማጠናከርና የህዝቦችን  አብሮነት ለማጎልበት በይቅርታና አንድነት  ላይ ስኬታማ ተግባራትን ማከናወን በመቻሉ በትጥቅ ትግል የተሰማሩ ሃይሎች ሳይቀሩ ወደ ሠላማዊ የትግል መስመር  ተመልሰዋል፣ ቀድሞ ጽንፈኛ ተብለው የተለዩ በውጭ አገራት የሚገኙ ሚዲያዎች  ወደ አገር ቤት ተመልሰዋል፣ በተለያየ ምክንያት በቁጥጥር ሥር የነበሩ በአሥርት  ሺህዎች  የሚቆጠሩ  የህግ ታራሚዎች በአገሪቱ  ህግ መሠረት በይቅርታ መፈታት  በመቻላቸው  የአገሪቱ  የፖለቲካ  ውጥረት ሙሉ በሙሉ መፍትሄ አግኝቷል ባይባልም ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች  መታየት ጀምረዋል።

 መንግሥት  ዴሞክራሲውን ለማጠንከር  እየወሰደ  ያለው  ዕርምጃ  ተስፋ ሰጪ መሆኑን የተገነዘበው  ኅብረተሰብ  ከጫፍ እስከ ጫፍ በነቂስ ወጥቶ  ለመንግሥት ያለውን  አጋርነትና ድጋፍ  በይፋ  አረጋግጧል።

የሃሳብ ብዙሃነትን ማስተናገድ ዋነኛው የዴሞክራሲያዊ መንግሥት መግለጫ ባህሪይ ነው፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ መንግሥት በአገሪቱ  የዴሞክራሲ ሥርዓት  እንዲጎለብት እና  የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ  የመገናኛ ብዙሃን ሥራቸውን በነጻነት እንዲከውኑ  ሁኔታዎችን  በማመቻቸቱ  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአገራችን  ማዲያዎች  ሚዛናዊ መረጃዎችን  ወደ ህዝብ ከማድረስ  ባሻገር  ለሚስተዋሉ  ችግሮች  መፍትሄ ጠቋሚ ወደመሆን  ደረጃ በመሸጋገር ላይ ናቸው።

በቅርቡ በማረሚያ ቤቶች አካባቢ በህግ ከለላ ሥር ባሉ ዜጎች ላይ  ይፈጸም የነበረ  አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ወደ ህዝብ ጆሮ እንዲደርስ  በማድረጋቸው መንግሥት  አፋጣኝ  መፍትሄ  እንዲሰጥ ጫና መፍጠራቸው አይነተኛ ማሳያ ነው። ሚዲያዎች ወደ ትክክለኛ  መስመር  መግባት መጀመራቸው የሚበረታታ በመሆኑ  በቀጣይም ከህዝብ የተደበቀ  ምንም ዓይነት ሚስጢር  ባለመኖሩ ሚዲያው የጀመረውን  የአገሪቱን ዴሞክራሲ ሥርዓት የማጎልበት  ጥረት  አጠናክሮ  ሊገፋበት   ይገባል። 

አንዳንድ ቡድኖችና ግለሰቦች  ህዝቦች እያካሄዱ  ያሉትን  ለውጥ  ለማደናቀፍ  አሁንም  ዘመኑን ያልዋጀ፣  የ21ኛው ክፍለ ዘመን  አስተሳሰብን  የማይመጥን  ያረጀና ያፈጀ ፖለቲካ  አካሄድን በመከተል ላይ መሆናቸው የአደባባይ ሚስጢር  ነው።

ኢትዮጵያዊያኖች የግጭት፣ የደባና የመመሳጠር የፖለቲካ አካሄድ የሚያስከትለውን ጉዳት፣ ከሌሎች ሳይሆን በራሳቸው  ደርሶ  የሚያውቁት በመሆኑ እንዲህ ላለው የመጠላለፍ  አካሄድና  የወደቀ አስተሳሰብ ቦታ ሊሰጡት በፍጹም አይገባም። 

ባለፉት  አንድ መቶ ዓመታት የተገበርነው  “የእኔ ብቻ  ትክክል  ነው”  የሚል የፖለቲካ አካሄድ  ኢትዮጵያን  ምን ያህል  የኋልዮሽ እንድትጓዝ እንዳደረጋት  የሚረሳ አይደለም። መንግሥት ነባራዊ የኢትዮጵያን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋትና  የመጫወቻ ህጉን ለሁሉም ሃይሎች እኩል  ለማድረግ  ቀን ከሌት በመታተር ላይ ነው፡፡ ይሁንና ይህ የመንግሥት ቀና አካሄድ ለአንዳንድ ሃይሎችና ግለሰቦች ምቾት ስላልሰጣቸው ዛሬም ከደባ ፓለቲካዊ አካሄድና አስተሳሰብ  አልተላቀቁም። 

በእንዲህ ያለ  ኋላ ቀር  የፖለቲካ አካሄድና  አስተሳሰብ የተዘፈቁ ሃይሎች ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት ከሚያደርጓቸው ሴራዎች ባሻገር ህዝቦች በለውጥ ሂደቱ ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው መሯሯጥ ከመንግሥትና ህዝብ ዕይታ የተሰወረ እንዳልሆነ ሊያውቁት ይገባል። 

 

መንግሥት እየተፈፀሙ ያሉ የፖለቲካ ደባዎችን በሆደ ሰፊነት ማለፍን የመረጠው  አገራዊ  መግባባትንና አንድነትን ለማጎልበት ካለው  ጽኑ አቋም እንጂ  እየተፈፀሙ ያሉት  የፖለቲካ ቅሌት  ተጠያቂነትን  የማያስከትሉ  ሳይሆኑ ቀርተው  አይደለም። 

 

መንግሥት የጀመረውን የዴሞክራሲ ምህዳሩን የማስፋት ሂደት አጠናክሮ ከመቀጠል ጎን ለጎን በእንዲህ ዓይነት እኩይ ተግባር ውስጥ የተዘፈቁ  ሃይሎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ  እያሳሰበ የህግ የበላይነትን የማስከበር ጉዳይ  ለድርድር የማያቀርብ መሆኑን  በዚህ  አጋጣሚ  በድጋሚ  ይገልጻል።

 

 የተጀመረው የይቅር ባይነት፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የመደመር ጉዞ  ቀጣይነት እንዲኖረው ኅብረተሰቡ እስካሁን ያደርግ  የነበረውን  ድጋፍና ትብብር አጠናክሮ  እንዲቀጥል  መንግሥት ጥሪውን  ያቀርባል።