የጨፌ አሮሚያ ስምንተኛ መደበኛ ጉባኤ ተጀመረ

በክልሉ የህግ የበላይነት በማረጋገጥ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ከዳር ለማድረስ ወሳኝ ስራዎች ማከናወን እንደሚገባ የጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ እሸቱ ደሴ አሳሰቡ፡፡

የጨፌ አሮሚያ አምስተኛ የስራ ዘመን ሶስተኛ ዓመት ስምንተኛ መደበኛ ጉባኤ  ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀመረ፡፡

በክልሉ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ እንዲረጋገጥና በአፈጻጸም ውስጥ የታዩ ክፍተቶችን በመለየት ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

ጨፌው የአባላቱን አቅም በመገንባት በተለይ የወረዳዎችና የከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች የማስፈጸም አቅም ለማጠናከር  ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

በዚሀም በአስፈጻሚው ዘንድ የሚታዩ የህግ ጥሰቶችና አሰራሮችን እንዲታረሙ በማድረግ ረገድ የጎላ ሚና እንደነበራቸው ገልጸዋል፡፡

የህግ የበላይነት በማረጋገጥ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ከዳር ለማድረስ የሚያስችሉ ወሳኝ ስራዎች ማከናወን እንዳሚገባ ያመለከቱት አፈ ጉባኤው፤ ይህንን ተግባር ህዝብና መንግስት ተቀናጅተው በቁርጠኝነትና በሙሉ አቅም መረባረብ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ለውጡን ለመቀልበስ የሚደረጉ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች ለማምከንና እንቅፋቶችን ለማስወገድ ህዝቦችን በማሰለፍ እንሰራለንብለዋል፡፡

በህዝብና በመንግስት መካከል ያለውን ጠንካራ ትስስር በሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ በማረጋገጥ እውን መሆን እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

በመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ የሚታዩ መጓተትና የጥራት ችግሮች አሁንም የህብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ክፍተቶች ሆነው በመቀጠላቸው ልዩ ትኩረት ሰጥተን መረባረብ አለብንብለዋል፡፡

በመንግስት መዋቅር የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራርና ኪራይ ሰብሳቢነት ሊወገዱ ያልቻሉ እንቅፋቶች በመሆኑ ህዝቡ በሙሉ አቅሙ መረባረብ እንደሚገባውም አመልክተዋል፡፡

በክልሉ ሰላምና የህግ የበላይነት እንዳይረጋገጥ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በመታገል የጨፌው አባላት ከህዝቡ ጋር በመሆን የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ጉባኤው ለሶስት ቀናት በሚያደርገው ቆይታ 2010 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም፣ የቀጣዩ ዘመን የመነሻ እቅድ፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ፍርድ ቤትና የጠቅላይ ኦዲት መስሪያ ቤት የስራ ክንውኖች ሪፖርት፣ 2011 የስራ ዘመን ማስፈጸሚያ በጀትና በሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በመምከር ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡(ኢዜአ)