የድንበር አለመግባባቱን በዘላቂነት ለመፍታት የትግራይ ክልል መንግስትና ህዝብ ከኤርትራ ህዝብ ጎን ይቆማል

የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ግጭትን በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረትን ለመደገፍ የትግራይ ክልላዊ መንግስት እና የትግራይ ህዝብ ከኤርትራ ህዝብ ጎን እንደሚቆም የክልሉ መንግሥት አስታወቀ ።

በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል  የተፈረመውን የሰላምና የወዳጅነት ስምምነት አስመልክቶ የትግራይ ክልላዊ መንግስት መግለጫ አውጥቷል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ለ20 ዓመታት የዘለቀው ሰላምም ጦርነትም የሌለበት ሁኔታን በዘላቂነት ለመፍታት በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የቀረበውን ወሳኔ ተከትሎ ህወሓትና የትግራይ ክልል መንግስትም በተመሳሳይ አኳኋን የትግራይ እና የኤርትራ ህዝቦች ወንድማማችነት ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ ይሠራል ።

የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግስታት የሁለቱ ህዝቦች ሰላም በዘላቂነት ለመፍታት እያሳዩት ያለው ዝግጁነትና ተነሳሽነት የክልሉ መንግስት እንደሚያደንቅም አስታውቋል።

በተለይ የኤርትራ ህዝብ ለ20 ዓመታት የዘለቀውን ሁኔታ በመፍታት የኢትዮ-ኤርትራ ወንድማማችንትና ወዳጅነትን ለማጠናከር ያሳየው ፍላጎት፣ ጉጉትና ፍቅር እጅግ የሚያስደስትና ከፊት ለፊታችን ብሩህ ተስፋ እንዳለውም የሚገለፅ ነው ብሏል መግለጫው ።

በመሆኑም የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ለኤርትራ ህዝብ ያለው ወንድማዊ አድናቆት ከፍ ያለ መሆኑን በመግለጫው ጠቁሟል ።

የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች የተጀመረውን ሰላም የማረጋገጥ ሥራ ይበልጥ ለማጠናከር በአጭር ጊዜ ውስጥ ቀጥተኛ የሆነ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በመጀመር ወንድማማችነታቸውንና ወዳጅነታቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪው አቅርቧል።