ዶክተር አብይ አህመድ ባለፉት 100 ቀናት በሰሩ ስራዎች የብሔራዊ መግባባት መፈጠሩ አስደስቶናል- የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባለፈት 100 ቀናት በሀገሪቱ በሰሩ የሰላምና ፀጥታ ስራዎች የብሔራዊ መግባባት መፈጠሩ እንዳስደሰታቸው የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

ዶክተር አብይ አህመድ ሀገሪቱን መምራት ከጀመሩ አንድ መቶ ቀናት ቢሆንም በሀገር ደረጃ ቀጣይነት ያለውን ለውጦች እያመጡ በመሆናቸው ደስተኛ ነን ሲሉ አስተያየታቸውን ለዋልታ የሰጡ የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህዝቦች የሚፈልገውን ሠላምና ዲሞክራሲ ለማስፈን ባደረገው ጥረት የነበረውን የፀጥታ ችግር በመቅረፍ በሀገሪቱ በአጭር ጊዜ ሰላም እንዲሰፍን አድርጓል ያሉት ነዋሪዎቹ የየራሳችን ሀሳብ በነፃነት እንድንገልጽ አድርጎናል ብለዋል፡፡

ባለፉት አንድ መቶ ቀናት የዲሞክራሲ መንገድ እንዲሰፋና ሁሉም ህብረተሰብ እኩልነቱን እንዲያረጋግጥ በሁሉም አካባቢ ተንቀሳቅሶ የሀገራዊ አንድነትን ማምጣት እንደቻሉም ተናግረዋል፡፡

ሁሉም አካላት እየታየ ያለውን ለውጥ ለማስቀጠል ከመደገፍ ባሻገር ለውጡ ከራስ እንደሚጀምር ተገንዝበው እያንዳንዱ ግለሰብ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚገባ የጠቆሙት ነዋሪዎች ድጋፋቸውን በተግባር ላይ ለማሳየት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች የመጣውን ለውጥ የማይፈልጉ አካላት እንዳሉ በመገንዘብ ህብረተሰቡ ነቅተው እንዲጠብቁም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡