ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የላቀ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ሥራ ተከናውኗል

ዶክተር አብይ አህመድ የጠቅላይ ሚንስትርነትን ኃላፊነት ተረክበው ማገልገል ከጀመሩበት ባሉት የ100 ቀናት ውስጥ አገሪቱ የላቀ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ሥራ መከናወኑን  የኢፌዴሪ የውጭ  ጉዳይ  ሚንስትር አስታወቀ ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም በዛሬው ዕለት በሠጡት ጋዜጣዊ  መግለጫ እንደገለጹት ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ  በዛሬው ዕለት 100 ቀናት እንደሞላቸውንና በዚህ ጊዜ ውስጥ ውጤታማ የሆኑ የተጋጋሉ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲያዊ ሥራ አከናውነዋል ብለዋል ።

ጠቅላይ  ሚንስትር  ዶክተር  አብይ ከኤርትራ ጋር ለ20 ዓመታት ያህል የዘለቀው የጦርነት ደመና ገፈው ሁለቱም ህዝቦች አሸናፊ የሆኑበት ፍቅርና ሰላም ነግሰው ጥላቻና አልህም  እንዲረቱ  የላቀ  አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን በመግለጫው አመልክተዋል ።

የኢትዮ -ኤርትራ  ጉዳይ ያለማንም ጣልቃ ገብነትና ሽምግልና የሁለቱ አገራት መሪዎች  በአሥመራ  የጋራ  የወዳጅነትና  ትብብር  ስምምነትንም  በመፈጸም የልዩነት ግንቡን ማድረሳቸውን   ቃልአቀባዩ  ገልጸዋል ።

እንደዚህ  አይነት  ታሪክ  በአንድ ጠቅላይ  ሚንስትር  የ100 ቀናት  ሥራ ብቻ  ይሆናል  ብሎ  ማንም  እንዳላሰበና በዚሁ አጋጣሚ ሁለቱ  መሪዎች  ይህን በማድረጋቸው  የዓለም አቀፍ  ዕውቅናና የሰላም  ሽልማት  ይሠጣቸው የሚልም አስተያየት ከወዲሁ እየተሠጠ ስለመሆኑ  ቃል አቀባዩ  ተናግረዋል ።

ኢትዮጵያና ኤርትራ  አሁን  አለመግባባቶቻቸውን  ፈተው  ወደ ሰላምና ፍቅር   መግባታቸውም በተባባሩት  መንግሥታት  ድርጅት ፣ ኢጋድ፣ የአፍሪካ  ህብረት፣ የአውሮፓ  ህብረት እና እንደ አሜሪካ ፣ ሩሲያ፣ ቻይና ፣ ቱርክ   አድናቆትና ድጋፍ እየተሠጠው ይገኛል ብለዋል  ቃልአቀባዩ ።

የውጭ ጉዳይ  ሚንስቴር ባለፉት ሦስት  ወራት  በጠቅላይ ሚንስትር  ዶክተር አብይ አህመድ አማካኝነት በተሠሩት የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ እንዲሁም የዜጋ  ዲፕሎማሲ  ሥራዎች ትልቅ ውጤት ማስመዝገቡን አስታውቋል ።