የአማራ ክልል 10ኛ መደበኛ ጉባኤ መካሄዱን ቀጥሏል

የአማራ ብሄራዊ ክልል ምክር ቤት 5 ኛ ዙር 3 ኛ ዓመት የስራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤ እንደቀጠለ ነው፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ስለ ክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ በምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር በአማራ ክልል ሰላም እንዳይሰፍንና የህግ የበላይነት ተጥሶ ስርዓት አልበኝነት እንዲነግስና የደገፍነው ለውጥ እንዲጠፋ የሚፈልግ የውጭ ኃይል የለም ጥፋቱም ልማቱም የሚወሰነው በእኛው ነው  ብለዋል ፡፡

በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ሰላም እንዲናጋ ህወሓት ምክንያት ሊሆን አይችልም፤መወቀስም መሞገስም ካለበት ክልሉ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ከመጠን በላይ በበዛ ጥላቻ የአማራ ክልልን ለማመስ የሚደረገው ጥረት መልሶ ራሱን ወደ ጥፋት የሚያመራ ድርጊት መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ለምክር ቤቱ እንደገለጹትም የአማራ ክልል ሰላም እንዲደፈርስ የብአዴን የቀድሞ አመራሮች ምክንያት ሊሆኑ እንደማይችሉ ገልፀው ለክልሉ ጥፋትም ሆነ ልማት ተጠያቂዎች እኛ ነን ብለዋል፡፡

በደብረ ማርቆስ ከተማ የተከሰተው ብጥብጥ ራስን በራስ የማጥፋት እንቅስቃሴ እንደሆነም አንስተዋልነው፡፡ ስለሆነም በአሁኑ ወቅት እጅን መቀሰር የሚያስፈልግበት ጊዜ አይደለንም ብለዋል፡፡

የክልሉ ህዝብ ቆም ብሎ ማሰብ አለበት ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ በተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ሰላምን ማደፍረስ ሳይሆን በሰከነ መንገድ ሰላምን ማምጣት የሁላችን ድርሻ ሊሆን ይገባል ማለታቸውን የአመራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ዘግቧል ፡፡