የኤርትራ ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት ለማጠናከር ታሪካዊ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናገሩ ።
ፕሬዚደንቱ ኢሳያስ በእሳቸው ለተመራው ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የኢትዮጵያና ኤርትራ ሕዝቦች ፍቅራቸውን መግለጽ ችለዋል ብለዋል ።
ይህን የሁለቱን ሕዝቦች ፍቅር ሳያዩ በህይወት ያለፉ ሰዎች እንዳሉ የጠቆሙት ፕሬዚደንት ኢሳያስ እኛ ይህን የሁለቱን ህዝቦች ፍቅር በህይወት ዘመናችን ማየታችን እድለኛ ያደርገናል ብለዋል ።
የሁለቱ አገራት ሕዝቦች ታላቅ የሰላምና ወዳጅነት የተቀመጠለትን ግብ እንዲመታ በጋራ መሥራት እንደሚገባ የገለጹት ፕሬዚደንት ኢሳያስ ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች ሁለት ህዝቦች ናቸው የሚል ሃቁን የማያውቅ ብቻ ነው ብለዋል ፕሬዚዳንቱ ።
ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማና አካባቢው ነዋሪ በእሳቸው ለሚመራው የልዑካን ቡድን ባደረገላቸው ደማቅ የህዝብ አቀባበል እጅግ ደስተኛ ከመሆናቸው የተነሳ ስሜታቸውን መግለጽ እንደተሳናቸው ተናግረዋል ።
በአጠቃላይ ከልብ የመነጨ ፍቅራቸውን እየተገለጹ ላሉት የኢትዮጵያ ኤርትራ ሕዝብም ታላቅ ምስጋና ከማቅረባቸውም በተጨማሪ ለሁለቱም አገር ህዝቦች የእንኳን ደስ አላቸሁ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል ።
ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበኩላቸው የአዲስ አበባና በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ለኤርትራ ልዑካን ቡድን ላሳያው ታላቅ ፍቅር ምስጋና አቅርበዋል ።