በፍቅርና በሰላም ስንደመር ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገን መስራት እንችላለን —ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

በፍቅርና በሰላም ስንደመር ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገን መስራት እንችላለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።

በሚሊኒዬም አዳራሽ በተካሄደው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሰላም ማብሰሪያ መድረክ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በፍቅርና በሰላም ስንደመር ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገን መስራት እንችላለን ብለዋል።

የሁለቱ አገራት ለየብቻ መኖር ግንጥል ጌጥ ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲደመሩ ግን ለምስራቅ አፍሪካና ለአፍሪካ ፈርጥና ጌጥ ናቸው ብለዋል።

ሁለቱ አገራትን መለያየት የሚችል አንዳች ኃይል የለም መልካችን ፍቅራችን ደግነታችን ጀግንነታችን አንድ አይነት ነው፡፡

የአገራቱ መደመር ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ስጋት ሳይሆን ተስፋ፣ ጦርነት ሳይሆን ልማት፤ የሚቀንስ ሳይሆን የተገኘው ሰላም ለሁሉም የሚጠቅምና ሁሉም በጋራ ሊጠብቀው የሚገባው መሆን ይኖርበታል።

ነጻነትና ሰላም በነጻ ሳይሆን ህይወታቸውን በፍቃድ ለገበሩ እና አካላቸውን ባጎደሉ ጀግኖች የተገኘ ነውና ሊጠበቅ ይገባልም ብለዋል።

ብዙ ስንገብር የመጣን ቢሆንም ለውጡን ለማቆም የሚችል አንዳች የሞት ኃይል የለም።

ጤንነታችን፣ ዴሞክራሲያችን እንዳያመልጠን ሰላማችን እንዳይወሰድብን ሁላችንም በአንድ ልብ ተደምረን ዘብ ልንቆም ይገባል።

ያንተ መኖር የኔ ዋስትና ፤የኔ መኖር ያንተ ዋስትና በማለት ኢትዮጵያና ኤርትራ መታረቃቸው ሲሰማ የኢትዮጵያ የቦንድ ዋጋ ለንደን ላይ ዋጋው መጨመር ጀምሯል።

ገና ያሰብናቸው የልማት ሥራዎች ሳንናገር በመታረቃችን ብቻ የኢትዮጵያ ዋጋ ከፍ ያለ ወደ ተሟላ ስርዓት ስንገባ የበለጠ እንደሚጠናከር እምነታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያና የኤርትራ የእርቅ ጉዳይ ለጓደኛሞች፣ለቤተሰብና ለጎረቤት ትምህርት ይሆናል ብዬ አምናለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደ ኢትዮጵያ ሊተያይ ይገባል ።

የኤርትራ ህዝብ በአስመራ የአዲስ አበባ ህዝብም በነቂስ ወጥቶ  ለኤርትራ ያለውን ፍቅር ያሳያበት ሰለሆነ ሰለ ደግነታችሁ፣ስለሰራችሁት ገድል ምስጋናና እናንተን ማገልገል ለእናንተ መስዋዕት መሆን  ከክብር በላይ ክብር ነው ብለዋል።

ነጻነት፣ሰላም፣ዴሞክራሲነና ፍቅር ከብርሃን እንጂ ጨለማ አያመነጨውም ፤ጨለማም ከእነዚህ ጉዳዮች ጋር አይስማማም፤ ስለሆነም የተገኘውን ሰላም፣ዴሞከራሲና  ነጻነት መጠበቅ ያሰፈልጋል ብለዋል።

የምንደመረው ለፍቅርና ለይቅርታ ብቻ፣ለሌሎች ተስፋ ለመሆን፣የጥላቻ ግንብን ማፍረስ ነው፣እኔና ኢሳያስ ስንደመር ሁለት ሳይሆን እኛ ለመሆን ይሁን ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል። (ኢዜአ)