“የኢትዮጵያና ኤርትራን ሰላምና የጋራ ልማት ማንም ኃይል እንዲፈታተነው አንፈቅድም” ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ

“በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተፈጠረውን ሰላምና የሚታሰበውን የጋራ ልማት ማንም ኃይል አንዲፈታተነው አንፈቅድም” ሲሉ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያሰ አፍወርቂ ገለፁ።

በኢትዮጵያ የሶስት ቀናት ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የኤርትራው ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፍወርቂ በሚሊኒዮም አደራሽ በተደረገላቸው የአቀባበል ስነስርዓት ላይ ንግግር አድርገዋል።

ፕሬዝዳንቱ “የኤርትራ ህዝብ ሰላምታና ፍቅር ለኢትዮጵያ ህዝብ ይዤ መጥቻለሁ” ሲሉ ንግግራቸውን ጀምረዋል።

በባህላችን መሰረት “ጥላቻን  አስወግደን ልማትና ብልፅግና ለማምጣት በሁሉም መስኮች ተባብረን ወደፊት ለመራመድ ቆርጠን ተነስተናል” ብለዋል።

“የትኛውም ኃይል ሰላማችንና ፍቅራችንን ለማወክ፣ የጋራ ልማታችንና ዕድገታችንን እንዲያሸብርና እንዲፈታተነን አንፈቅድም” ሲሉም በአፅንኦት ተናግረዋል።

“በጋራ ጥረታችን ባለፈው ችግር የከሰርነውን አስመልሰን ወደፊት ሁሉንም ነገር እናሸንፋለንም ነው ያሉት አቶ ኢሳያስ።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ በማድነቅም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።(ኢዜአ)