በአዲስ አበባ የኤርትራ ኢምባሲ በይፋ ተከፈተ

በአዲስ  አበባ  የሚገኘው  የኤርትራ  ኢምባሲ  የኢትዮጵያና የኤርትራ  መሪዎች  በተገኙበት  በዛሬው  ዕለት በተካሄደ  ደማቅ ሥነ ሥርዓት  በይፋ  ተከፍቶ ሥራ ጀምሯል  ።

የኤርትራ  ኢምባሲ  የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድና  የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ  በተገኙበት  የኤርትራ  ብሔራዊ  መዝሙር  ተዘምሮ  የኤርትራ  ሰንደቅ ዓላማ  በኢምባሲው እንዲውለበለብ ተድርጓል ።

ሁለቱ አገራት  ወደ ግጭት  ከገቡ በኋላ ለ20 ዓመት ያህል ዝግ  የነበረው በአዲስ አበባ የኤርትራ  ኢምባሲ  በዛሬው ዕለት  እድሳቱ  ተጠናቆ እንዲከፈት ተደርጓል ።

ጠቅላይ  ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ  ከሳምንት በፊት በአሥመራ ባደረጉት ጉብኝት  ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ጋር ሁለቱ አገራት ኢምባሲዎቻቸውን እንዲከፍቱ  ያደረጉትን ስምምነት   ተከትሎ  ነው  የኤርትራ  ኢምባሲ እንዲከፈት የተደረገው ።

ኢትዮጵያም በስምምነቱ መሠረት በቅርቡ በአሥመራ ኢምባሲዋን እንደምትከፍትም   ተገልጿል ።