ህብረተሰቡ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ግጭት ለማስነሳት ለሚፈልጉ አካላት ተባባሪ እንዳይሆን ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ ጠየቁ ።
ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ በዛሬው ዕለት በአገሪቱ ጉብኝት ሲያደርጉ የነበሩትን የኤርትራው ፕሬዚዳንትን በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደማቅ አሸኛኘት አድርገውላቸዋል ።
ከሽኝቱ በኋላ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ በሠጡት መግለጫ እንደገለጹት የአዲስ አበባና አካባቢዋ ነዋሪዎች እንዲሁም የሐዋሳ ነዋሪዎች ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ላደረጉት ደማቅ አቀባበልም ታላቅ ምስጋና አቅርበዋል ።
ጠቅላይ ሚንስትሩ በመግለጫቸው ህብረተሰቡ በአንዳንድ አካባቢዎች ግጭትና አለመረጋጋት እንዲከሰት ለሚፈልጉ አካላት ትብብር እንዳያደርግም ጥሪ አድርገዋል ።
በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች እየተከሰቱ የሚገኙት ግጭቶች ከተጀመሩት የፍቅርና የመደመር ጉዞ ጋር አብረው የማይሄዱ በመሆናቸውም በአፋጣኝ መቆም እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚንስትሩ አጽዕኖት ሠጥተው ተናግረዋል ።
በሶማሌና አሮሚያ አካባቢዎች ግጭቱ የቀጠለ መሆኑን በመጠቆም በርካታ ንጹሐን ሰዎች እየሞቱ ነው ፣ ግጭቱን ለጊዜው ማስቆም ባይቻል እንኳን ህብረተሰቡ በሁኔታው ተባባሪ ባለመሆን ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጠይቀዋል ።
የአዲስ አበባ ፖሊስና የፌደራል ፖሊስ ግጭት ሊያስነሱ የሚችሉ አካላትን በመቆጣጣር ረገድም ተገቢውን ሥራ እያከናወነም እንደሚገኝም ጠቅላይ ሚንስትሩ በመግለጫቸው አመልክተዋል ።
ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ በግል የውጭ ገንዘቦችን ይዘው የሚገኙ ሰዎች ወደ ባንክ ሄደው እንዲመነዝሩ ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚንስትሩ መንግሥት በሂደት በሚወስደው እርምጃ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል ።