ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ለኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት መሻሻል የመሪዎቹን ቁርጠኝነት አደነቁ

ለኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት በፍጥነት መሻሻል የሁለቱ አገራት መሪዎች ያሳዩት ቁርጠኝነት ሊመሰገንና ሊደነቅ እንደሚገባ የኢፈዲሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ተናገሩ።

ፕሬዝዳንቱ ዛሬ ማለዳ በብሄራዊ ቤተ-መንግስት ለመሪዎቹ የቁርስ ግብዣ አድርገዋል።

በመርሃ-ግብሩ ለኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ቦታዎች የሚያሳዩ የቅርጻ ቅርጽ ስጦታዎች ተበርክቶላቸዋል።

ፕሬዝዳንት ሙላቱ በዚሁ ወቅት ሁለቱ መሪዎች በአገራቱ ሰላምን ለማምጣት ያሳዩት ቁርጠኝነትና በአጠቃላይ እያደረጉ ላለው እንቅስቃሴ ምስጋና ቸረዋል።

ከዚህ በፊት ”በተለያዩ የውጭ አገራት ተወክለው የነበሩ የኤርትራና ኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች እየተዋወቁ እንደማይተዋወቁ ሲሆኑ ኖረዋል” ነው ያሉት።

ከዚህ በኋላ መሰል መራራቆች ቀርተው ወንድማማችነት ዳግም ታውጇል ያሉት ፕሬዝዳንቱ ሁሉም ዜጋ ባለበት ለተግባራዊነቱና ለጋራ ጥቅም ሊተጋ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ የነበሩት የኤርትራው ፕሬዝዳት ኢሳይያስ አፈወርቂ ዛሬ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ አስመራ ተመልሰዋል፡፡ (ኢዜአ)