የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች በአጎራባች አካባቢዎቻቸው የፌዴራል የፀጥታ አካላት ገብተው የማረጋጋት ሥራ እንዲሰሩ ተስማሙ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒሰትር ዶክተር አብይ አህመድ  በሠጡት ትዕዛዝ መሠረት የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሳና መስተዳደሮች በክልሎቹ አጎራባች አካባቢዎች የፌዴራል የፀጥታ አካላት በአፋጣኝ ገብተው የሰላምና መረጋጋት ሥራ እንዲሰሩ ተስማሙ። 

ጠቅላይ ሚኒሰትር ዶክተር አብይ አህመድ አልፎ አልፎ የሚታየው የዜጎች ሕይወት መጥፋት እንዲቆም፣ ይህንን የሚያባብሱ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ፣ በአጠቃላይ አሁን የተፈጠረውን ብሩህ ተስፋ ለማስቀጠል በፍቅርና አብሮነት ሕዝቡ እንዲተጋ፤ ከዚህ በተቃራኒው የሚፈጸሙ ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶችን ለመከላከል የኢፌዴሪ መከላኪያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ ሕግ የማስከበር ሥራቸውን በኃላፊነት ስሜት እንዲወጡ ትዕዛዝ መስጠታቸው ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒሰትሩ የሠጡትን መመሪያ ተከትሎም የኦሮሚያ ክልል ርዕስ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር ውይይት አድርገዋል።

በውይይታቸውም ግጭት በተፈጠርባቸው አጎራባች አካባቢዎች የፌዴራል የፀጥታ ኃይል በመግባት የጸጥታ፣ የሠላምና መረጋጋት ሥራ እንዲሰራ፤ እንዲሁም የሕግ ማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ መስማማታቸውን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት  በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ለአፈጻጸሙ የሁለቱም ክልል የመንግሥት መዋቅሮች ከፌዴራል የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ችግሩን ለመፍታት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚወጡ ርዕሳና መስተዳደሮቹ ማረጋገጣቸውን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ገልጸዋል።

በተለይ የሕግ-ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እንደሚሠራና የሁለቱም ክልል ሕዝብ እንደወትሮው የለውጥ ሂደቱን በመጠበቅ ለመፍትሄው ኃላፊነቱን በተገቢው መንገድ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል። 

በቀጣይ በበርካታ እሴቶች የተሳሰረውን የሁለቱ ክልል ሕዝብ ከመሰል ግጭቶች በመከላከል ለዘላቂ መፍትሄ፣ ለሰላምና ፍቅር አብሮ የሚሠራበትን ሁኔታ ለማስቀጠል ተከታታይ የሕዝብ ለሕዝብ ኮንፍረንሶችን በአፋጣኝ ለማካሄድም ርዕሰ መስተዳደሮቹ ወስነዋል።(ኤፍቢሲ)