የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ሠራተኞች በዛሬው ዕለት ሥራ ጀመሩ

የሥራ  ማቆም  አድማ ያደረጉት  የአዲስ አበባ ከተማ ቀላል  ባቡር  ሠራተኞች በዛሬው ዕለት  ሥራ  መጀመራቸውን  አስታወቁ ።

የቀላል ባቡር ሠራተኞቹ ከ3ዓመት በላይ የቆየ መብቶቻቸውንና ጥቅማጥቅሞቻቸው ለማስከበር ለኮርፖሬሽኑና ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ አቅርበው ምላሽ በማጣታቸው ምክንያት በትናንትናው ዕለት የሥራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን መግለጻቸው ይታወሳል  ።

ሠራተኞቹ ያልተመለሱላቸውን ጥያቄዎች ለኮርፖሬሽኑ ማቅረብ እንደሚቀጥሉ በመግለጽ የቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚ የሆነው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ እንግልት እንዳይደርስበት ሥራቸውን በዛሬው ዕለት መጀመራቸውን ገልጸዋል ።

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ  አስፈጻሚ ዶክተር ብርሃኑ በሻህ  በበኩላቸው ሠራተኞቹ ያነሱት ጥያቄ አግባብነት የጎደለው መሆኑን  ተናግረዋል ።

ሠራተኞቹ ጥያቄያቸውን ማቅረብ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ 90 በመቶ የሚሆነው  ጥያቄያቸው ምላሽ  መሠጠቱንና   ሠራተኞቹ  የሚያነሱት ጥያቄዎች ሌላ  ዓላማን ያነገበ በመሆኑ  ኮርፖሬሽኑ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገድድ ገልጸዋል ።

ሠራተኞቹ  በበኩላቸው  በተለያዩ  ጊዚያት ያነሷቸው  ጥያቄዎች በአግባቡ አለመመለሳቸውን በማስረጃ ጭምር ማቅረብ እንደሚችሉና ጥያቄያቸው ከሌላ ዓላማ  ጋር  ሊያያዝ እንደማይችል  ለዋልታ ተናግረዋል  ።

የኮርፖሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደረጄ ተፈራ ኮርፖሬሽኑ ከሠራተኞቹ ጋር   ስምምነት ላይ  በመድረሱ  በዛሬው  ዕለት  ቀላል  ባቡሩ  አገልገሎት መሥጠት  መጀመሩን  አስረድተዋል ።