የኢትዮ-ኤርትራን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ማጠናከር ያስፈልጋል- የባድመ ከተማ ነዋሪዎች

የኢትዮ-ኤርትራን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ማጠናከርና የሰላም ውይይት መጀመር ወሳኝ መሆኑን አስተያየታቸውን የሰጡ የባድመ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ነዋሪዎቹ እንዳሉት በኢትዮጵያና በኤርትራ መንግስታት መካከል የተደረሰውን እርቀ ሰላም ተከትሎ አሁን የተጀመረው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

በየደረጃው ህዝብን መሰረት ያደረገ የሰላም ውይይት መድረክ በአፋጣኝ መጀመር እንዳለበትም ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል ከ20 ዓመታት በላይ የቆየው የቅራኔ መንፈስ ተወግዶ በምትኩ ሰላምና እርቅ ወርዶ ለጋራ ተጠቃሚነት መስራት መጀመሩ ከልብ እንዳስደሰታቸውም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

አገራቱ ለጋራ ሰላም ስምምነት በመድረሳቸው የተፈጠረባቸው የደስታ ስሜት ዘላቂ እንዲሆን የሁለቱ አገራት ህዝቦች በተለይ በሰላም ጉዳይ  የሚወያዩበት ዕድል መኖር እንዳለበት የገለጹት አቶ በርኸ እስቂያስ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ ናቸው።

የተደረሰበትን የሰላም ስምምነት የሁለቱም አገራት ህዝቦች ከልብ ተቀብለው ተግባራዊ እንዲያደርጉ በተለይ በድንበር አካባቢ የህዝቦች የፊት ለፊት የውይይት መድረክ መፈጠር ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

የ70 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋና የባድመ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ማንጠግቦሽ ፀሐዬ በበኩላቸው “ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው፤ ሰላም ካለ የመኖር እድሜም ይጨምራል፤ ሁለቱም መንግስታት የ20 ዓመት የሰቆቃ ጊዜ በሰላምና በፍቅር እንዲተካ በማድረጋቸው የተሰማኝ ደስታ የላቀ ነው‘‘ ብለዋል።

”በሁለቱም መንግስታት የተጀመረው የሰላም፣ የእርቅና የፍቅር መድረክ ለዓመታት በህዝብ ሲነሳ የነበረን ጥያቄ በአግባቡ የመለሰ የዲፕሎማሲ ውጤት ነው” ያለው ደግሞ የባድመ ነዋሪ ወጣት ሃብቶም መሰለ ነው።

በመንግስታቱ መካከል የተጀመረው የእርቅና የሰላም ውይይት የብዙዎችን ትኩረት የሳበ ቢሆንም ይህንን በጎ ጅምር ለማጠናከር በአሁኑ ወቅት የተጀመረው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በቀጣይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል። (ኢዜአ)