በህገ-ወጥ መንገድ ከአገር ሊወጣ የነበረ 10 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ በቁጥጥር ስር ዋለ

በተለያዩ መንገዶች 10 ሚሊዮን ዶላር በህገወጥ መንገድ ከአገር ለማውጣት ሲሞከር በቁጥጥር ሥር መዋሉን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማል እንደገለጹት ህብረተሰቡን ባሳተፈና በተጠና መልኩ በብሄራዊ መረጃና ደህንነት፣ ከአዲስ አበባና ከኦሮሚያ ፖሊስ ጋር በመሆን በተለያዩ አካባቢዎች በጥቂት ቀናት ውስጥ በተከናወነ ዘመቻ ገንዘቡ ከአገር ሳይወጣ ተይዟል።

ድርጊቱን ፈጽመዋል የተባሉት ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳዩ እየተጣራ ይገኛል፡፡

ህገወጥ የገንዘብ ዝውውሩን ለመከላከል የተጀመረው ዘመቻ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያመለከቱት ኮሚሽነሩ፤ በዛሬው ዕለት በሞጆና በአዳማ መካከል በተካሄደ ዘመቻ 570 ሺህ ዶላር መያዙን በአብነት አንስተዋል።

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ፤ ባለፉት ጥቂት ቀናት በተካሄዱ ዘመቻዎች የጦር መሳሪያ በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር በቁጥጥር ስር ውሏል። ከአንድ ሺህ በላይ የነፍስወከፍ መሳሪያ እና 80 ሺህ በላይ ጥይቶች ተይዘዋል።

አዲስ አበባ ከተማ ትናንት በተካሄደ ዘመቻ 234 ሽጉጥ 17 ሺህ ጥይት መያዙንም ነው ኮሚሽነሩ ያመለከቱት።

አርማጭሆ 298 ሽጉጥ፣ ሸኖ 53 ሽጉጥ፣ ጋምቤላ 32 ክላሽንኮቭ፣ ሁለት መትረየስ፣ ሰሜን ሸዋ 20 ሽጉጥ እና አንድ መትረየስ መያዙንና ተጠርጣሪዎቹም በቀጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።

የዶላርን ከአገር በህገወጥ መንገድ ማስወጣትና የጦር መሳሪያ ዝውውሩትስስር ሊኖራቸው ይችላልየሚል ጥርጣሬ መኖሩን የተናገሩት ኮሚሽነር ዘይኑ፤ በገንዘቡ መሳሪያ በመግዛትና በማስገባት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለመረጋጋት ለመፍጠር የታለመ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአገሪቷን ኢኮኖሚ ለማዳከም የሚፈጸም አሻጥር እንደሚመስልም ነው የተናገሩት።

ደሴ አካባቢ 24 ሚሊዮን ብር መያዙን አውስተው፤ ተጠርጣሪዎቹ  “ከአንድ ባንክ አውጥተን ወደ ሌላ ባንክ ልናስገባነውየሚል ምላሽ መስጠታቸውን ገልጸዋል።

ሆኖም አካሄዱ ህገወጥነት ያለው በመሆኑ በጉዳዩ ላይ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ ከፖሊስና ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ወንጀለኞችን በማጋለጥ ዘመቻው እንዲጠናከር እንደዚህ ቀደሙ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ጥሪ አድርገዋል።(ኢዜአ)