ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከፍተኛ ሜዳሊያን ተሸለሙ

 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና የኤርትራው ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ታሪካዊ የሰላም ስምምነት እንዲደረስ ላበረከቱት አስተዋፀኦ በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች አልጋወራሽ ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ነኸያን የሀገሪቱን ከፍተኛ ፕሬዚዳንታዊ ሜዳሊያ ተሸለሙ።

በዚህ የሽልማት ስነ ስርዓት ላይም የሀገሪቱ የተለያዩ ሚኒስትሮች፣ ተቀማጭነታቸውን በአቡ ዳቢ ያደረጉ አምባሳደሮች እና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ተገኝተዋል።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኤርትራ ጉብኝት በማድረግ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መጀመሩ የሚታወስ ነው።

በዚህም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው የጀመሩ ሲሆን፥ በተለያዩ ጉዳዮችም ስምምነት ላይ መድረስ ችለዋል።

ይህንን ተከትሎ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያሰ አፈወርቂ በኢትዮጵያ ለሶስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት አድርገዋል።

በጉብኝታቸውም በኢትዮጵያ የኤርትራ ኤምባሲን መርቀው የከፈቱ ሲሆን፥ የኢትዮጵያ አየር መንገድም ወደ አስመራ በረራ መጀመሩ የሚታወስ ነው።