በአገሪቷ አንዳንድ ማረሚያ ቤቶች መለቀቅ አለብን በሚል ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ማድረግ ተቀባይነት የለውም- መንግስት

በአገሪቷ አንዳንድ ማረሚያ ቤቶች መለቀቅ አለብን በሚል ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ማድረግ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ታራሚው ሕግና ስርዓትን አክብሮ መንቀሳቀስ እንዳለበት መንግሥት አሳሰበ።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

አቶ ካሳሁን እንደገለጹት “መንግሥት በማረሚያ ቤት ያለውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ለማሻሻል በጥናት የተደገፈ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል።”

በቅርቡም የይቅርታ አዋጁን መነሻ በማድረግ በሺዎች የሚቆጠሩ ታራሚዎች መለቀቃቸውን አስታውሰው፤ የምህረት አዋጁን ሥራ ላይ ለማዋልም ከጫፍ ተደርሷል ብለዋል።

ይሁን እንጂ የይቅርታና የምህረት አዋጁን ተከትሎ በአንዳንድ ቦታዎችና ታራሚዎች ዘንድ መለቀቅ አለብን በሚል ሕጋዊ ያልሆኑ ተግባራት እየተስተዋሉ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም በቂሊንጦና ቃሊቲ በጩሄት ማረሚያ ቤቱን ማወክ፣ በአርባ ምንጭ ማረሚያ ክሊንክ ላይ ጉዳት ማድረስ፣ በደብረ ማርቆስ ወልድያና ፍኖተ-ሠላምም በተመሳሳይ ህግን ያልተከተሉ ተግባራት ታይተዋል ነው ያሉት።

”መሰል እንቅስቃሴዎች መንግሥት ‘በጊዜ የለኝም’ ቅኝትና ስሜት እየፈጸማቸው ያሉትን የለውጥ ሥራዎችን ጭምር ወደ ኋላ የሚጎትቱ ናቸው” ያሉት አቶ ካሳሁን፤ ያልተፈቀደ የይቅርታና የምህረት አዋጅ ተጠቃሚ ለመሆን የሚደረግ ሙከራ ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።

በማረሚያ ቤቶች የታራሚዎች አያያዝ ላይ ከዚህ በፊት የነበሩ ክፍተቶች እንዳይደገሙ መንግሥት አበክሮ እንደሚሰራ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው ከማረሚያ ቤት በጉልበትና ህግን በመጣስ ለመውጣት መሞከር ተገቢ እንዳልሆነና በዚህ ድርጊት የሚሳተፉ ታራሚዎች ህጉን ሊያከብሩ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

እንደ አቶ ካሳሁን ገለጻ በአንዳንድ ማረሚያ ቤቶች የተስተዋሉ አለመረጋጋቶች በመንግስት እልባት እያገኙ ነው። (ኢዜአ)