ኢንጂነር ስመኘው በቀለ በጥይት ተመተው ህይወታቸው ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ

የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ በጥይት ተመተው ህይወታቸው ማለፉን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ጀኔራል ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማል በኢንጂነር ስመኘው በቀለ አሟሟት ዙሪያ በዛሬው ዕለት  ለጋዜጠኞች መግለጫ በሠጡት  ወቅት  እንደገለጹት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ በጥይት  ተመተው  ህይወታቸው ማለፉን  ተናግረዋል ።

ኮሚሽነር በሰጡት መግለጫም ኢንጂነር ስመኘው ከጆሯቸው በስተጀርባ በኩል በጥይት  በመመታታቸው ነው ህይዎታቸው እንዳለፈ  ገልጸዋል።

አሁን ላይም ፖሊስ ጉዳዩ ለማጣራት የተለያዩ አሻራዎችንና ማስረጃዎችን በመውሰድ እያጣራ ይገኛል ብለዋል።

ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው ኢንጂነር ስመኘው ጠዋት  ላይ  ቢሮ እንደነበሩም መረጃ እንዳለ ጠቅሰዋል።

የአስክሬን ምርመራ በጳውሎስ ሆስፒታል እየተደረገ መሆኑን የገለፁት ኮሚሽነሩ የፎሬንሲክና የአሻራ ምርመራ በሳይንሳዊ መንገድ እየተካሄደ ነው ብለዋል።

ፌደራል  ፖሊስ   ወንጀል  ተፈጽሞባቸዋል ተብለው በሚጠረጠሩ  አካባቢዎች  በአጠቃላይ  ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል እንዲሁም የምርመራ ሥራ እየተደረገ መሆኑን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል ።

ህብረተሰቡ የምርመራ ውጤቱ በአግባቡ ተከናውኖ ለህዝቡ ይፋ እስኪደረግ ድረስ በትዕግስት  እንዲጠባበቅ ጥሪ አድርገዋል ።

የፖሊስ አባላትም ጉዳዩን ለማጠራት ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ እንደሆነ ነው ኮሚሽነሩ የጠቆሙት።