ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ ጋር ተወያዩ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የአሜሪካውን ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስን በዋይት ሀውስ አግኝተው ተወያዩ።

በውይይታቸው ላይ ምክትል ፕሬዚዳንት ፔንስ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ እያከናወኑት ስላለው ማሻሻያ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።

በተለይም በሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ በቢዝነስ ምህዳሩ ላይ እንዲሁም በኢትዮጵና ኤርትራ መካከል ሰላም በመፍጠሩ ረገድ የፈፀሟቸውን ማሻሻያዎች አድንቀዋል።

በዚሁ ወቅት አሜሪካ ለኢትዮጵያ ልማት የምታደርገውን ድጋፍ እንደትምቀጥልም አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአሜሪካ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተው ለመወያየት በአሜሪካ ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪም የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም/አይ ኤም ኤፍ/ ኃላፊ ክርስቲን ላጋርድ ጋርም በተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት ተገናኝተው ተወያይተዋል።

በዚህ ውይይታቸው ላይም ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ሊኖር በሚችለው የአይ ኤም ኤፍ ድጋፍ ዙሪያ መነጋገራቸውን በውይይት ላይ የተገኙት የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍፁም አረጋ ተናግርዋል።

ኃላፊዋ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለተፈራረሙት የሰላምና ወዳጅነት ስምምነት መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለያዙት የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳም አድናቆታቸውን ገልፀዋል።(ኤፍቢሲ)