ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ትውልድን የመቅረጽ ሃላፊነት አለባቸው- ጠ/ሚ አብይ አህመድ

በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እውቀትና ክህሎታቸውን ተጠቅመው  ትውልድና ህብረተሰብን  ለመልካም  ሃላፊነት ማነጽ እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሳሰቡ።

በሎስ አንጀለስ ከተማ ሐምሌ 22 ቀን የኢትዮጵያ ቀን ሆኖ እንዲከበር ተወስኗል

“የተሰጠንን ሁሉ ጥለን ባዶ እጅ ማጨብጨብን ለመቀየር በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግና የመደመር እሳቤ ምርጥ ምርጡን መቀነስ ሳይሆን ምርጥ ምርጦቹን በመመለስ ታላቅ መሆን ነው” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ገልዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የገዳ ስርዓትን ለዓለም ያስተዋወቀች ሀገር ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ብርቅ ሊሆንባት አይገባም” ሲሉም ተናግረዋል።

በሎስ አንጀለስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም “የመንግስትን ጥረት እንደግፋለን” ብለዋል።
ፕሮፌሰር አለማየሁ ኃይለማርያም ኢትዮጵያን በመወከል “ጥላቻን አቁመን የመንግስትን የማሻሻያ ጥረት እንደግፋለን” ሲሉም ተናግረዋል።

ዶክተር አብይ ከሎስአንጀለስ ተጠባባቂ ከንቲቫ ቪያል ሬጎሳ ጋር  ውይይት ካደረጉ በኋላ በሎስ አንጀለስ ከተማ ሐምሌ 22 ቀን የኢትዮጵያ ቀን ሆኖ እንዲከበር መወሰኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

በሎስ አንጀለስ የተካሄዱት ሶስት መድረኮች ተጠናቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይ ወደ ሚኒሶታ የሚያቀኑ ሲሆን በነገው ዕለት በከተማዋ ከኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የዋሽንግተን ዲሲ ከንቲቫ ሙሪየል ቦውሰር ሐምሌ 21 ቀን የኢትዮጵያዊያን ቀን ሆኖ እንዲታሰብ ባወጁት መሰረት የዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ሐምሌ  21 ቀን ”የኢትዮጵያውያን ቀን” ሆኖ እንዲሰየም መወሰኑም የሚታወስ ነው። (ኢዜአ)