ቅዱስ ሲኖዶስ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ እና ብፁዓን ሊቀነ ጳጳሳት ላይ የተላለፈውን ቃለ ውግዘት አነሳ

የኢትዮጵያ ኦርቶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ እና ብፁዓን ሊቀነ ጳጳሳት ላይ የተላለፈውን ቃለ ውግዘት ማንሳቱን አስታውቋል።

ሶኖዶሱ በሰሜን አሜሪካ ሲኖሩ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ እና ሌሎች ብፁዓን ሊቀነ ጳጳሳት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ደማቅ አቀባባል እንደሚደረግላቸው ገልጿል።

የኢትዮጵያ ኦርቶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉዳዩን አስመልክቶ ትናንት መግለጫ ሰጥቷል።

የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ስራ አስኪያጅ ብጹዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ቤተክርስቲያኗ አንድነቷን ጠብቃ ለአገሪቱ ሰላምና ደህንነት ብዙ ሰርታለች።

ከሁለት አስርት አመታት ወዲህ ያልተጠበቁ ችግሮች ተፈጥረው በቤተክርስቲያኗ አባቶች መካከል መለያየት መፈጠሩን ያስታወሱት አቡነ ዲዎስቆሮስ፤ የነበረው መለያየት ለውግዘት በሚዳርግ ደረጃ ደርሶ እንደነበር ተናግረዋል።

ቅዱስ ሲኖዶሱ ተወያይቶ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መወሰኑን ተከትሎ በተለያዩ ጊዜያት ተላልፈው የነበሩ ቃለ ውግዘቶችን ማንሳቱን ገልጸዋል።

በቤተክርስቲያኒቱ ተከስቶ ከነበረው ልዩነት በፊት የተሾሙ ሊቃነ ጳጳሳት በውጭ አገርም ሆነ በአገር ቤት በቅዱስ ሲኖዶሱ አማካኝነት ተመድበው እንዲያገለግሉ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

በተያያዘ ዜና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ እና ብጽዓን አበው ሐምሌ 25 ቀን 2010 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ የገለጹት አቡነ ዲዮስቆሮስ፤ የቤተክርስቲያኒቱ ምዕምናን ከጠዋቱ 12 ሰዓት በቦሌ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት አቀባባል እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ዕለቱ የቤተክርስቲያኒቱ በዓል በመሆኑ በቤተክርስቲያኒቱ ህግና ቀኖና መሰረት ደማቅ የአቀባበል ስርዓት እንደሚደረግም ተናግረዋል።

የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች እንዲሁም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ወጣቶች በተገኙበት ቅዳሜ ሐምሌ 27 ቀን 2010 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ ደማቅ የአቀባበል ዝግጅት እንደሚደረግም አክለዋል

ሁሉም ሰው የቤተክርስቲያኒቱን ህግና ስነምግባርን በተከተለ መልኩ እንዲሁም ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን ተላብሶ በአቀባበል ተሳታፊ እንዲሆንም ጥሪ አቅርበዋል።

ቅዱስ ሲኖዶሱ እርቀ ሰላሙ እንዲወርድ ያላሰለሰ ጥረት ላደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ  ምስጋና አቅርበዋል።(ኢዜአ)