ፍርድ ቤቱ በሰኔ 16ቱ የቦምብ ፍንዳታ የተጠረጠሩ 10 የፖሊስ ኮሚሽን አባላት የክስ መዝገብን ተመለከተ

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የአዲስ አበባ ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳ ባሉበት መዝገብ የተጠረጠሩ 10 የኮሚሽኑ አባላት መዝገብን ተመልክቷል፡፡ ፍርድቤቱ  በትናንት ችሎቱ  ተጨማሪ የሶስት ቀናት የጊዜ ቀጠሮም ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው ችሎት ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ከዚህ በፊት ያሰባሰባቸውን መረጃዎችና ማስረጃዎች እንዲሁም የምርመራ ሂደቶችን ለፍርድ ቤቱ አቅርቦ አለማጠናቀቁን ገልጿል፡፡ በዚህም ተጨማሪ የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል፡፡

የአዲስ አበባ ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳን ጨምሮ ሌሎች ተጠርጣሪዎችም የተጠየቀው የጊዜ ቀጠሮ አሳማኝ ያልሆነና እጅግ የበዛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ በእስር በቆዩባቸው ባለፉት 36 ቀናት ተገቢውን ምርመራ ማጠናቀቅ ነበረበት ፤ይሕንም አላከናወነም ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በዚህም የጠየቁት የዋስትና መብታው ተከብሮ ከውጭ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የግራ ቀኙን የተመለከተው ፍ/ቤቱ  ፖሊስ ለአምስተኛ ጊዜ ያቀረበው ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ተገቢ አለመሆኑን በመጥቀስ በአጭር ጊዜ ስራውን አጠናቆ መዝገቡን ለአቃቤ ህግ ማስረከብ እንዳለበት አስገንዝቧል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የፖሊስ አባላት በመሆናቸው በዋስትና ቢለቀቁ የምርመራ ስራው ላይ  አሉታዊ ጫና ስለሚኖረው ፍርድ ቤቱ የዋስ መብት ጥያቄያቸውን አልተቀበለም፡፡

ለመርማሪ ፖሊስም ለመጨረሻ ጊዜ የሶስት ቀናት የጊዜ ቀጠሮ በመስጠት መዝገቡን ዘግቷል፡፡