ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ በአሜሪካ የነበራቸው ቆይታ እጅግ የተሳካ እንደነበር ገለጹ

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ በአሜሪካ  ሦስት  ግዛቶች  ያደረጉት ቆይታ አድካሚ ቢሆንም  እጅግ የተሳካ እንደነበር  ገልጸዋል  ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ በዛሬው ዕለት በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ  ከፍተኛ  የመንግሥት  ባለሥልጣናት  ደማቅ አቀባበል  አድርገውላቸውዋል ።

ጠቅላይ  ሚንስትሩ ቦሌ አለም አቀፍ  አውሮፕላን ማረፊያ  በደረሱበት  ወቅት  በሠጡት  ጋዜጣዊ  መግለጫ እንደገለጹት  በአሜሪካ በነበራቸው  ቆይታ  ምን ያህል  የአገራቸውን  ፍቅር  የተራቡ  መሆኑን  ያሳዩበት  መሆኑን  ተናግረዋል ።

የአሜሪካ ቆይታቸው ኢትዮጵያውያን አንድ እንዳንሆን  የለያየን የጥላቻ፣ የመናናቅ፣ የራስ ወዳድነትና የቂም በቀል ግንብ  እንዲፈርስ በጎ ሚና የተጫወተ እንደነበር ጠቅላይ  ሚንስትሩ አመልክተዋል ።

የኢትዮጵያውያን  የአንድነት ድልድል አሁን  መገንባት ተጀምሯል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ  በአሜሪካ  የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ቀደም ሲል  የነበረውን  የልዩነት  መንፈስ ለመናድ  እንደሚችሉ በተግባር  አሳይተዋል ብለዋል ።

በአሜሪካ  የሚገኙ ኢትዮጵያውያን  ከኢትዮጵያውያን ለሄደው የልዑካን ቡድን ያደረጉት አቀባበል  እጅግ   አስገራሚ  እንደነበር  የጠቆሙት  ጠቅላይ ሚንስትሩ አገራቸውን  በፍቅርና በታማኘነት ለማገልገል  ያላቸውን  ፍላጎት በእጥፍ እንዲጨምር ማድረጉን  ገልጸዋል ።

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪየስ  4ኛ  ፓትሪያርክ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው  በራሱ  በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን  ውስጥ  የነበረውን  ልዩነት  ግንብ  ሙሉ በሙሉ በማፍረስ  በተግባር መረጋገጡን  የታየበት እንዲሁም ይህም  ለሁሉም  እምነተ  ተከታዮች  ደስተና ክብረ መሆኑን  ገልጸዋል ።

ጠቅላይ  ሚንስትር ዶክተር  አብይ  በአሜሪካ  ቆይታቸው  ከግንቦት 7 የአርበኞች  ግንባር አመራሮች  ጋርም  እጅግ ውጤታማ ውይይት  ማድረጋቸውንና  የግንቦት 7 አባላት  አገራቸውን በሰላማዊ መንገድ  የማገልግል ፍላጎት እንዳላቸውንና በአገሪቱ በፖለቲካው፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚያው ዘርፎች ለመሥራት  እንደሚፈልጉም አረጋግጠዋል ብለዋል ።

የኢትዮጵያን መንግሥት በመቃወም የሚታወቀው  ጀዋር መሐመድም ከጥቂት ቀናት  በኋላም ወደ አገሩ  በመግባት  ከህዝብ  ጋር እንደሚቀላቀል  ገልጸዋል ።

 በተጨማሪም  ታማኝ  በየነም  ከዓመታት  ቆይታ በኋላ ወደ አገሩ  ተመልሶ አገር  የመገንባት  ፍላጎቱንለመወጣትፍላጎት እንዳለው አረጋግጧል ብለዋል  ጠቅላይ ሚንስትሩ  በመግለጫቸው ።

ጠቅላይ  ሚንስትሩ  በሜኔሶታ ከኦሮሞና አማራ  ኮሚኒቲ ጋር ውይይት  እንደነበራቸው  በመግለጽ  የአገሪቱ ሕዝቦች እርስ በራስ በመቀራረብ ችግሮችን በመፍታት  ኢትዮጵያን  አንድ በማድረግ  በኩል ሁሉም ተገቢውን  ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል ።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከእንግዲህ በኋላ አንዱ ብሔርና ሃይማኖት ሌላኛውን ብሔርና ሐይማኖት የሚያጠቃባት  እንዳትሆንና  ሁሉም  በራሱ ብሔርና ሃይማኖት ተከብሮ በጋራና በአንድነትነ በፍቅር የምንኖርባት አገር  እንድትሆን  እያንዳንዱ ዜጋ አገር የመገንባት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል ።