በወታደራዊ ስነምግባር ጥሰትና በኩብለላ ለተከሰሱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ምህረት ተደረገ

በወታደራዊ ስነ ምግባር ጥሰትና ኩብለላ ወንጀሎች ለተከሰሱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ምህረት ማድረጉን የመከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽንና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀኔራል ኪዱ አለሙ፥ እንደገለጹት መንግስት በሃገር አቀፍ ደረጃ የጀመራቸውን የለውጥ እንቅስቃሴዎች ለማስቀጠል መከላከያ ሰራዊት ለውጡን በመደገፍ እየሰራ ነው።

በዚህም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ያጸደቀውን የምህረት አዋጅ መሰረት በወታደራዊ የስነ ምግባር ጥሰት ተከሰው በማረሚያ ቤት የሚገኙና ቀደም ሲል ከሃገር የኮበለሉ የሰራዊት አባላት ምህረት ተደርጎላቸዋል ብለዋል።

የምህረት አዋጁ የሚመለከታቸው የሰራዊት አባላት ተቋሙ ባዘጋጃቸው አካባቢዎች ባሉ ጽህፈት ቤቶች በአካልም ሆነ በተዘጋጀ ፎርም ማመልከት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።

በዚህም በተቋሙ አዲስ አበባና አካባቢዋ የሚገኙ ታራሚዎች ቤላ አካባቢ በሚገኘው የፍትህ ዳይሬክቶሬት ጽህፈት ቤት ሪፖርት ማድረግ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

ከአዲስ አበባ ውጭ ላሉ ታራሚዎች ባሉበት ክልል በተጠባባቂ የፍትህ ዳይሬክቶሬት ጽህፈት ቤት ሪፖርት ማድረግ የሚችሉ ሲሆን፥ በወረዳና በዞን ላሉ ደግሞ በዞኑ በሚገኘው ጽህፈት ቤት ሪፖርት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

በዚህም ከዛሬ ጀምሮ በአዲስ አበባ ጽህፈት ቤቱ ፎርሙን ማስሞላት እንደተጀመረ ጠቅሰው፥ በክልሎች ደግሞ ከነሃሴ አንድ ቀን ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ ሪፖርት ማድረግ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ሪፖርት አድርገው ያላጠናቀቁ ታራሚዎች የጊዜ ገደቡ ሲጠናቀቅ ሪፖርታቸው ተቀባይነት እንደማይኖረውም አሳስበዋል።(ኤፍ ቢ ሲ)