የአርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም ሥርዓተ ቀብር በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈፀመ

የአንጋፋው  የአርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም  ሥርዓተ ቀብር በዛሬው ዕለት በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን   ተፈጸመ ።

የአርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም ሥርዓተ ቀብር ላይ  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት ባለስልጣናት፣ አጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አድናቂቆቹ እና የጥበብ ሰዎች በተገኙበት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል።

አርቲስት ፍቃዱ ተክለማሪያም በህይወት ዘመኑ ያበረከታቸው በርካታ ዘመን አሽሬ ሥራዎቹና የህይወት ታሪኩ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ  ላይ  ተነቧል።

አርቲስት ፍቃዱ በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የቲቢ አምባሳደር ተደርጎ በተሾመበት ወቅት በርካታ ሥራዎች  ለአገሩ እንዳበረከተም  ተገልጿል ።

አርቲስቱ ለበርካታ ዓመታት በነገሰበት የብሄራዊ ትያትር መድረክም የሞያ ባልደረቦቹ ፣ቤተሰቦቹ ፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና አድናቂዎቹ በተገኙበት በዛሬው ዕለት ከ5 ሰዓት ጀምሮ ለአርቲስቱ አስከሬን የአሸኛኘት መርሃ ግብር ተዘጋጅቶለት ስንብት ተደርጎለታል፡፡

ፈቃዱ ተክለ ማርያም የሚወደው እና አክብሮና ተክብሮ የኖረበትን ሞያውን ብዙ ባየበት የስነ ጥበብ  ቤቱን ሲሰናበት የሞያ ባልደረቦቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹ እናአድናቂዎቹ እንባቸውን እያፈሰሱ ሸኝተውታል ።

አርቲስት ፍቃዱ  ባደረበት የኩላሊት ህመም ሲሰቃይ የቆየ  ሲሆን  በፀበል ሲረዳ ቆይቶ ሐምሌ 24 ቀን 2010 ዓ.ም አመሻሽ ላይ በ62 አመቱ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ይታወሳል ።

አርቲስት ፈቃዱ ከሚታወቅባቸዉ ተውኔቶች ውስጥ ቴዎድሮስ፤ንጉሥ ኦርማህ፣ ኦቴሎ፣ ኤዲፐስንጉሥ ፣ሐምሌት፣ የሰርጒ ዋዜማ እና ባለካባ ባለ ዳባ ጥቂቶቹ ሲሆኑ በቴሌቪዥን ከተሳተፋባቸው ድራማዎች መካከል ደግሞ ባለጉዳይ፣ ገመና እና መለከት ይገኙበታል፡፡  ጥቁር ደም እና ሳቤላ ደግሞ በሬድዮ ትረካ ማንሳት ይቻላል፡፡