ጠቅላይ አቃቢ ህግ በነ ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳ የተከፈተውን ክስን አጠናክሮ በ10 ቀናት የጊዜ ገደብ ለፍርድ ቤቱ እንዲያቀርብ ተወሰነ

የአዲስ አበባ  ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር የነበሩት ግርማ ካሳን ጨምሮ አስር ተጠርጣሪ የፖሊስ አባላትን በመርማሪ ቡድን  የተከፈተውን  ክስ  ዛሬ ከሰዓት በኋላ ተመልክቷል ።

ፍርድቤቱም  በዛሬው ዕለት ውሳኔው የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በምርመራ ቡድኑ  የታየውን ጉዳይ  አጣርቶና ክሱን አጠናክሮ ለፍርድ ቤት  እንዲያቀርብ የ10 ቀናት የጊዜ ገደብ ሠጥቶታል፡፡

አቃቢ ህግ በችሎቱ ጉዳዩን አጣርቶ ክስ ለመመሥረት የ15  ቀናት የጊዜ ገደብ እንዲሠጠው የጠየቀ ሲሆን  ፍርድቤቱ  የ10 ቀናት የጊዜ  ገደብ ሠጥቶታል ።

እስካሁን ድረስ ጉዳዩን  ለማጣራት  የተቋቋመው የምርመራ  ቡድን  በተቀመጠለት  የጊዜ  ገደብ  መሠረት  ውጤቱን   በዛሬው ዕለት ለአቃቢ ህግ አስረክቧል ።    

ቀደም ሲል  በጉዳዩ ጋር  በተያያዘ  በ10 ሰዎች ላይ  ክሱ የተከፈተ ቢሆንም 1አንድ ተጨማሪ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውለው በአሁኑ ወቅት በ11 ሰዎች ላይ ክሱ እየታየ እንደሚገኝም  በችሎቱ ተገልጿል ። 

ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም የድጋፍ ሰልፍ ሲካሄድ በደረሰው የቦንብ ፍንዳታ ወቅት የስራ ክፍተት በመፍጠር የተጠረጠሩት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር የነበሩት ግርማ ካሳን ጨምሮ አስር ተጠርጣሪ የፖሊስ አባላት  ላይ ምርመራ  እየተካሄደ  መሆኑን  ይታወቃል ። 

በሰኔ 16ቱ የቦንብ ጥቃት ቀጥተኛ ተሳትፎ አላቸው በሚል በተጠረጠሩ አምስት ግለሰቦች ላይ ክስ ሊመሰረት እንደሆነ መዘገባችን ይታወሳል፡፡