የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ የአዲስ አበባ ቢሮውን አስመረቀ

የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ (ኦ ኤም ኤን) የአዲስ አበባ ቢሮውን በይፋ አስመረቀ።

በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ የተገኘው ድል እንዳይደናቀፍ በትብብር ልንሰራ ይገባል ብለዋል።

አቶ ለማ በንግግራቸው የኦ ኤም ኤን አመራሮች በውጭ ሃገር ሲታገሉ መቆየታቸውን ጠቅሰው፥ አሁን ላይ ሃገር ቤት በመግባት ሊያግዙ በመምጣታቸው አብረው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አንስተዋል።

እስከዛሬ ለትግሉ መሰናክል የነበረውን ለማስወገድ አዲስ ምዕራፍ ላይ ነን ያሉት አቶ ለማ፥ አዲሱ ምዕራፍ ኦሮሚያን ብሎም ኢትዮጵያን የምናለማበትና የምናሳድግበት ስለሆነ ይህ ዳር እንዲደርስ መላው ህዝብ አስተዋጸኦ ሊያደርግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የተገኘው የድል ወደ ኋላ እንዳይመለስም በጥንቃቄ እና በትኩረት ከህዝቦች ጋር በጋራ በመተባበር ወደ ፊት ልናራምደው ይገባልም ብለዋል አቶ ለማ በንግግራቸው።

ጃዋር መሃመድን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ዜጎት ለህዝቡ ነጻነትና መብት ሲሉ በስደት ከሚኖሩበት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ከክልሉ ጋር ለመስራት በመወሰናቸው ምስጋና እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

ከዚህ በኋላ በፖለቲካ ምክንያት ህዝቡ መጋጨት የለበትም ያሉት አቶ ለማ፥ የፖለቲካ አመራሮችም ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ /ኦ ኤም ኤን/ ስራ አስኪያጅ አክቲቪስትና የፖለቲካ ተንታኝ ጃዋር መሃመድ በበኩሉ፥ ሃገሪቱ እዚህ ለውጥ ላይ እንድትደርስ ሁሉም አስተዋጽኦ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሷል።

ይህ ለውጥም የተፈለገው መንገድ ላይ እንዲደርስ ያለመዘናጋት በመደጋገፍና ጥላቻንና ጥርጣሬን በማስወገድ ሃገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ ይገባልም ብሏል።

ወጣቱ አሁን የታየው ለውጥ እንዲመጣ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደነበረው ጠቅሶ፥ ህግ የማስከበር ስራውን ለፀጥታ አካላት በመተው ወደ ልማት ፊታቸውን እንዲያዞሩም ጥሪውን አቅርቧል።

ጊዜው በመበታተንና በመለያየት ተራርቀን የምንቆምበት ሳይሆን ሃገሪቱ ወደተሻለ ዴሞክራሲ፣ ልማት፣ እኩልነት እና ፍትህ የሰፈነባት እንድትሆን መላው ህዝብ አመራሩን በማድመጥ የለውጡ ሞተር ሆኖ እንዲቀጥልም ጥሪውን አስተላልፏል።

ከዚህ ባለፈም ማንኛውም አካል ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ ይጠበቅበታልም ነው ያለው።

የአማራ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ደግሞ፥ ኦ ኤም ኤን የአማራ እና የኦሮሚያን ህዝብ አንድነት እና ወንድማማችነት በማጠናከር ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደነበረው አስታውሰዋል።

አሁን በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ለውጥ አንድነትን፣ ፍቅርን፣ መተባበርን፣ ይቅርታን በህዝቡ ዘንድ በማስፋት ቂም በቀል፣ ጭቆና እና በደልን ቦታ ያሳጣ መሆኑንም ገልጸዋል።

እየመጣ ያለው ለውጥ እንዳይደናቀፍም ሚዲያው ህብረተሰቡን በማንቃት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው እንዲጠናከር የሚያደርገውን አስተዋጽኦ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል።

የአማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት ከኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ዎርክ ጋር በጋራ የመስራት ፍላጎት እንዳለው ጠቅሰው፥ ኦ ኤም ኤን በሃገሪቱ ለውጥ እንዲመጣ አስተዋጽኦ እንደነበረው ጠቁመዋል።

የኦህዴድ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው በሀገሪቱ እየመጣ ያለው ለውጥ ሁሉን አሳታፊና የእያንዳንዱ ሰው ጉዳይ ነው ብለዋል።(ኤፍ ቢ ሲ)