በጅግጅጋ ከተማ እየደረሰ ያለዉ ጥቃት አሳሳቢ መሆኑ ተገለፀ

በኢትዮጲያ ሶማሌ በጅግጅጋ ከተማ እየደረሰ ያለዉ ጥቃት አሳሳቢ መሆኑን በክልሉ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ኮሚሽነር ጀማል መሃመድ ገልጸዋል፡፡

በጥቃቱም በበርካታ ዜጎች ህይወት እና ንብረት ላይ አደጋ መድረሱን ኮሚሽነሩ ዛሬ በሰጡት በጋዜጣዊ መግለጫዉ አስታውቋል፡፡

ከጥቃቱ በስተጀርባ ያለው አካል አልታወቀም ያሉት ኮሚሽነሩ በክልሉ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ሙሉ በሙሉ መውደሙን ገልጸዋል፡፡

የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት መኪና፣ የተለያዩ ሰነዶችና ንብረቶችም እንደወደሙ አስታውቋል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ ምን ያህል ሰዎች እና ንብረት ላይ አደጋ እንደደረሰ ማጣራት ያልተቻለ ቢሆንም በቀጣይ በሚደረገው ተከታታይ የምርመራ ሂዴቶች በጥቃቱ ጀርባ ያሉትን አካላት እንዲሁም የደረሰውን አጠቃላይ ጉዳት ይፋ እንደሚያደርግ ኮሚሽነሩ አስታውቋል፡፡

በክልሉ የተፈጠረውን ችግር ለመቀልበስ የሚመለከተዉ አካል አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጥም ጥሪ አቅርበዋል፡፡