ወጣቶች በተረጋጋ መንፈስ በአገር ግንባታ ላይ እንዲያተኩሩ ከመንግስት ጎን ሆነን እንደግፋለን – አቶ ጀዋር መሐመድ

ወጣቶች በተረጋጋ መንፈስ አገር ግንባታ ላይ እንዲያተኩሩ ከመንግስት ጎን በመሆን እንደሚያበረታቱ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጀዋር መሐመድ ገለጹ።

ፕሬዘዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ የስራ ኃላፊዎችን ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው  አወያይተዋል።

የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ዳይሬክተር  አቶ ጀዋር መሐመድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ “ወጣቶች ያላቸውን እምቅ አቅም በአገሪቷ ልማት ላይ ማዋል አለባቸው”።

“በተለያዩ አገሮች ለበርካታ ዓመታት ያካበትነውን ልምድ ለወጣቶች በማካፈል በኢትዮጵያ አንድነትና ዘላቂ ሰላም ላይ የበኩላችንን እንወጣለን” ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማማከር ካልሆነ በቀር በኢትዮጰያ ፖለቲካ እንደማይሳተፉ የገለጹት አቶ ጀዋር ሙሉ ትኩረታቸው ሙያን መሰረት ያደረገ የሚዲያ ስራ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።

የሱማሌ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች የአመራሩ ድክመት እንጂ በህዝቡ መካከል ጥላቻ እንደሌለም ጠቁመዋል።

በመሆኑም አመራሩ በሚፈጥራቸው ዘርን መሰረት ያደረገ ክፍፍል የሚፈጠሩ ግጭቶች እንዲቆሙና በአገሪቷ ሰላም አንድነትና እድገት እንዲሰፍን አበክረን እንሰራለን ብለዋል።

ፕሬዘዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በበኩላቸው ዲያስፖራዎችን በማስተባበር ወጣቱ በአገር ግንባታ ላይ በንቃት እንዲሳተፍ በመንግስት ድጋፍ እንደሚደረግ መናገራቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የፕሬዘዳንት ጽህፈት ቤት የፕሮቶኮልና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ የስራ ሃላፊዎች ላመጡት ቀናኢ አስተሳሰብ ምስጋና አቅርበው፤ ለዚህ መሰሉ ተግባራትም ሰፊ የመንግስት ድጋፍ እንደሚኖር ነው የገለጹት።

በመሆኑም ኃላፊዎቹ የጀመሩትን ወጣቶችን አስተባብሮ ለስራ ማነሳሳትና የስራ አጥነትን የመቀነስ እንቅስቃሴ በፍጥነት መተግበር እንዳለባችው ጠቁመዋል። (ኢዜአ)