በሻሸመኔ ከተማ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ

በሻሸመኔ ለኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጀዋር መሐመድ በተደረገ አቀባበል ላይ በደረሰ አደጋ ሶስት ሰዎች ሲሞቱ 71 ሰዎች ቀላልና ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽነሩ አቶ አለማየሁ እጅጉ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደጠቀሱት ለድጋፍ የወጣው ሕዝብ ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ በተፈጠረ መጨናነቅና በኋላም በተከሰተ ችግር በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።

የወረዳው አስተዳደርና ጸጥታ ንብረት የነበረች አንድ መኪና ላይ ቃጠሎ መድረሱንም አስታውቀዋል።

በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ቦንብ የያዘች መኪና እንደተቃጠለች የሚገለጸው ከእውነት የራቀ መሆኑንና በስፍራው ጥቃት ለማድረስ እንደተያዙ ተደርጎ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት መፈጸሙን አስመልክቶ የተሰራጨውን መረጃ ፖሊስ አጣርቶ ወንጀለኞችን ለህግ ያቀርባል ብለዋል።

ሕዝቡም ከሚመለከተው አካል ትክክለኛ መረጃ እስኪያገኝ መጠበቅና ከፖሊስ ጎን በመሆን ሰላምና ጸጥታ የማስከበር ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባም እንዲሁ።

ፖሊስ ችግር እንዳይከሰትና ጉዳቱ እንዳይባባስ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው፤ ከስድስት ተጎጂዎች በስተቀር ሁሉም ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች የመጀመሪያ እርዳታ ተደርጎላቸው ወደየቤታቸው መመለሳቸውን አስታውቀዋል።

የሻሸመኔ ከተማ ህዝብ ወደተለመደው ማህበራዊ እንቅስቃሴ፤ ከተማዋም ወደመረጋጋት መመለሷን ገልጸዋል።

መንግስት ያደረገውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ ከውጭ አገር ለሚገቡ አካላት የተለያየ አቀባበልና ሰልፍ እንደሚደረግ ገልጸው፤ “ነገር ግን የሰላም ጥሪውን የማይቀበሉና ለውጡን ለማደናቀፍና ውዥንብር ለመፍጠር የሚፈልጉ ኃይሎች አሉ” ሲሉም ተናግረዋል።

በደረሰው ጉዳትና ሞት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ማዘኑን ገልጸው፤ ሁከት የሚፈጥሩና በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሱ አካላት በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆኑም አረጋግጠዋል። (ኢዜአ)