ደኢህዴን በክልሉ ዘላቂ ሰላምና መልካም አስተዳደር ለማስፈን የህዝብ መገልገያ ተቋማትን እያሻሻለ ነው

የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) በክልሉ ዘላቂ ሰላምና መልካም አስተዳደር ለማስፈን የህዝብ አገልግሎት መስጫ  ተቋማትን እያሻሻለ መሆኑን ገለጸ።

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም ስራም እየተከናወነ መሆኑን ድርጅቱ አስታውቋል።

በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ያለውን ነባራዊ ሁኔታና የደኢህዴን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያስቀመጠውን አቅጣጫ በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።

የደኢህዴን ሊቀ-መንበር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እንዳሉት፤ ህዝቡ እያነሳቸው ላሉት የመልካም አስተዳደር፣ የልማትና ተያያዥ ጥያቄዎች እንዲሁም በተሃድሶ ወቅት ተለይተው እርምጃ ያልተወሰደባቸውን ችግሮች በአጭር፣ መካከለኛና በረጅም ጊዜ ዕቅድ ምላሽ ለመስጠት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።

በክልሉ የዜጎችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ዘላቂ ሰላምና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የመሰረተ-ልማት አውታሮችን ጨምሮ የህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለማጠናከር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ እስከ ክልል ድረስ ያሉ የህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ማሳለጥ ቅድሚያ የሚሰጠው በመሆኑ ወደ ተግባር መገባቱን ነው ወይዘሮ ሙፈሪሃት የገለፁት።

በህብረተሱ በዋናነት የሚነሱት መሰረታዊ ጥያቄዎች ከመሰረተ ልማትና አገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ የወጣቶችን ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተደራጀና የነቃ የወጣቶች ተሳትፎ እንዲኖር ደኢህዴን ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።

በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውና የታመነባቸውን አመራሮች ወደ ስራ በማስገባት በአንዳንድ አካባቢዎች የሰላምና መልካም እስተዳደር ለውጦች ተመዝግበዋል ብለዋል።

በአመራር ስራቸው ላይ ችግር ፈጣሪዎችን ተጠያቂ ማድረግ የአቅም ክፍተት ያለባቸውን አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ማድረግ የድርጅቱ ቀጣይ የቤት ስራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚከሰቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የብሄር መልክ በመስጠት በህዝቦች መካከል መከፋፈልን የሚፈጥሩ አካላት እንዳሉ ገልጸው፤ “በዚህ ድርጊት የሚሳተፉ አደብ ሊገዙ ይገባል” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

ህዝቡ የፀጥታው ባለቤት ራሱ መሆኑን በመገንዘብ ለክልሉ ሰላምና ለአገራዊ አንድነት የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤና የደኢህዴን ሊቀ-መንበር ወይዘሮ ሙፈሪያት ጥሪ አቅርበዋል።

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን በፍጥነት መልሶ ለማቋቋም እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት ከምስራቅ ጉጂ ዞን የተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎች አብዛኞቹ ወደ ቀያቸው የተመለሱ ሲሆን ምዕራብ ጉጂ አካባቢ የተፈናቀሉትንም መልሶ የማቋቋም ስራ እየተከናወነ መሆኑን ወይዘሮ ሙፈሪሃት ገልጸዋል። (ኢዜአ)