የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚንስትርና የደህንነት ቢሮ ኃላፊ በሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ ውይይት ለማድረግ ዛሬ አዲስ አበባ ይገባሉ

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሽኩሪ እና የሀገሪቱ ደህንነት ቢሮ ሀላፊ ስለኢትዮጵያና ግብፅ መካከል ግንኙነት እና በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ውይይት ለማድረግ በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ ይገባሉ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ ኤል ሲሲ የተላከውን መልዕክት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያደርሳሉ ተብሏል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በተመለከተ እና ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በፈረንጆቹ 2015 በአባይ ወንዝ ዙሪያ ስለደረሱበት ስምምነት አፈፃፀም ውይይት ያደርጋሉ ነው የተባለው።

ከዚህ ባለፈ በሶስቱ ሀገራት ለመሰረተ ልማት  ኢንቨስትመንት የሚውል ፈንድ ለማዘጋጀት በሚቻልበት ሁኔታም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት ያደርጋሉ።

እንዲሁም የሶስቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባለፈው ግንቦት ወር በአሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች ላይ ስለደረሱባቸው ስምምነት ውይይት እንደሚያደርጉም ታውቋል።

በሀገራቱ መካከል የተደረሰው ስምምነት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የሚከታተል አለም አቀፍ ባለሙያዎችን ያካተተ ኮሚቴ ማዋቀር የሚያስችል እንደነበር ተነግሯል።

የሶስቱ ሀገራት መሪዎች በየስድስት ወሩ ለምክክር እንዲገናኙ በሀገራቱ መካከል በተደረሰው ስምምነት መግባባት ላይ መደረሱን አልሀራም በዘገባው አስታውሷል።(ኤፍቢሲ)