ተጨማሪ 6 የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በቁጥጥር ስር ዋሉ

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የቀድሞ ርእሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሃመድ ዑመር በተጨማሪ ሌሎች ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳባቸው 6 የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ምክር ቤት የቀድሞ የክልሉን ፕሬዝዳንት አብዲ መሃመድ ኡመርን ጨምሮ 7 ከፍተኛ አመራሮችን ያለመከሰስ መብት እሁድ እለት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤው ማንሳቱ ይታወሳል።

በዚህም መሰረት የክልሉ ቁልፍ አመራሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ዘይኑ ጀማል  አስታውቀዋል።

በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች በፍጥነት ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡና ሌሎች በቁጥጥር ስር ያልዋሉ ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው የክልሉ አመራሮችን በፍጥነት በቁጥጥር ስር ለማዋል እንደሚሰራም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተጨማሪ በአብዲ መሃመድ ዑመር እንደተቋቋመ የሚነገርለትሄጎየወጣት ቡድን አባላትና አመራሮች፤ እንደዚሁም ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ሰዎች ዝርዝር በማዘጋጀት የመለየት ስራ መሰራቱንም ኮሚሽነር ዘይኑ አስታውቀዋል።

በቁጥጥር ስር የዋሉት የክልሉ የቀድሞ ርእሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሃመድ ዑመር በክልሉ ፈፅመውታል ተብለው የተጠረጠሩባቸውን ወንጀሎች በተመለከተ ላለፉት 15 ቀናት በክልሉ የኢሶህዴፓ አመራሮች፣ የክልሉ ምሁራን፣ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት ውይይት የተካሄደ ሲሆን፥ በአመራሩ መሪነት አሰቃቂ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙ በውይይቱ ጎልቶ ወጥቷል።

ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ባለፈም አቶ አብዲ የህዝብን ሃብት ለግል ጥቅም በማዋል፣ በከፍተኛ ዝርፊያ፣ የመንግስት አሰራርን ወደ ጎን በመተው የህዝብ ሃብት በግለሰቦች እንዲዘረፍ በማድረግና በሌሎች በርካታ ወንጀሎች መጠርጠራቸውን ኮሚሽነር ዘይኑ ተናግረዋል።

የአብዲ መሃመድ ዑመር በቁጥጥር ስር መዋል ለኢትዮጵያ ብዙ ትርጉም እንዳለው የተናገሩት ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማል፥ ህዝብን በድሎ፣ የሰብዓዊ መብትን ረግጦ፣ የህዝብን ስልጣን ለግል ጥቅምና ዝና ከማዋልም ባለፈ ሰውን በመግደልና መስዋዕት በማድረግ በስልጣን እቆያለሁ ብሎ ማሰብ በኢትዮጵያ ውስጥ የማይቻል መሆኑን ያመላክታል ብለዋል።

ከዚያም ባለፈ የአቶ አብዲ መሃመድ በቁጥጥር ስር መዋል በኢትዮጵያ ውስጥ የህግ የበላይነት የማክበርና የማስከበር ጉዳይ ከጊዜ ወደጊዜ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ከመጠቆሙም ባለፈ የህግ የበላይነት አይመለከተንም ብለው የሚያስቡ ሰዎች ቆም ብለው እንዲያስቡ የሚያደርግ መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።(ኤፍ )