በአማራ ክልል በህዝብ ትግል የመጣውን ለውጥ ከዳር ለማድረስ ምሁራን እገዛ ማድረግ አለባቸው

በአማራ ክልል በህዝብ ትግል የመጣውን አዲስ የለውጥ ክስተት ከዳር ለማድረስ ምሁራን  በሳይንሳዊ ምርምርና በእውቀት ማገዝ እንደሚጠበቅባቸው የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አስታወቁ ።

ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ  አቶ ብናልፍ አንዷልም  ከአማራ ምሁራን ጋር በተደረገው የምክክር መድረክ ላይ  የአማራ ምሁራን በመደራጀት ለህዝባቸው መብትና ጥቅም መከበር መንቀሳቀስ መጀመራቸው አዲስ የለውጥ ክስተት ነው ብለዋል።

የተጀመረው ለውጥ በህዝብ ዘንድ ጫፍ እስከ ጫፍ ሙሉ ተቀባይነት ማግኘቱ ከዚህ ቀደም ያልታየ ክስተት መሆኑን ያነሱት የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ብናልፍ አንዱዓለም "ለውጡ የአማራን ህዝብ ከድህነት፣ ኋላቀርነት፣ ከአፈናና ጭቆና የሚላቀቅበት እንዲሁም በራሱ ጉዳይ ራሱ የሚወስንበትን ሰፊ እድል ፈጥሮለታል" ብለዋል ።

በህዝብ መስዋትናትና ትግል የመጣውን ለውጥ በሳይንሳዊ ምርምር በማገዝ ተጨማሪ እውቀትና አቅም በመፍጠር ከዳር በማድረስ እረገድ ምሁራን ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

ቀደም ሲል የአማራ ምሁራን ከብአዴንና ከክልሉ መንግስት ሆድና ጀርባ ሆነው በጥርጣሬ ሲተያዩ ቆይተዋል ያሉት ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ በዚህም በክልሉ መሰረታዊ ለውጥ ሳይመጣ መቆየቱን አስታውሰዋል ።

የክልሉ መንግስትም ሆነ ብአዴን እንቅስቃሴውን በሙሉ አቅም በመደገፍ የአማራን ህዝብ ጥያቄ በተሟላ መንገድ ለመመለስ ከመቸውም ጊዜ በተሻለ ዝግጁ መሆኑን ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል ።

"ለአማራ ህዝብ የሚያስፈልገው ፕሮፌሰርና ዶክተር ብቻ ሳይሆን እሰከገጠር ወርዶ የደሃውን ህዝብ ችግር በተጨባጭ የሚፈታ ነው" ያሉት ደግሞ ኮሎኔል ደመቀ  ዘውዱ ናቸው።

"በህዝቦች መካከል የሚስተዋሉ ልዩነቶችን የሚያሰፋ ሳይሆን ልዩነትን የሚያጠብ ምሁር መሆን ይገባል" ያሉት ኮለኔሉ "የሌሎች ወንድሞችን  ክብርና ስብዕናም መጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪ የሆኑት አቶ ባያብል አጥናፉ

"የተጀመረው ለውጥ ህዝብ በሚፈልገው መንገድ ተስተካክሎ እንዲሄድ ምሁራን መደገፍ አለብን " ሲሉም ገልፀዋል ።

በሃገሪቱ ለውጥ ውስጥ የአጭር፣ የመካከላኛና የረጅም ጊዜ እቅዶችን በመሳያት ወጣቱ ወደ አላስፈላጊ ጥፋት እንዳይገባ መምከር እንደሚገባ አመልክተዋል ።

"የአማራ ምሁራን የላቀ ተሳትፎ ለለውጡ ቀጣይነት፤ ለአማራ ህዝብ ዘላቂ ተጠቃሚነትና አገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ በሚካሄደው የምክክር ምክክር ላይ ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ ምሁራን እየተሳተፉ ነው።(ኢዜአ)