ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ጋር ተወያዩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎችን በቤጂንግ ተገናኝተው ውይይት አድርገዋል ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቻይና ቤጂንግ እየተካሄደ ባለው የቻይና አፍሪካ ፎረም ጎን ለጎን ነው የተቋማቱን መሪዎች አግኝተው ያወያዩት።

በትናንትናው እለትም ከዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።

በነበራቸው ቆይታም የዓለም ጤና ድርጅት የዓለም አቀፍ የጤና አገልግሎት ሽፋንን ለማሳደግ እየሰራቸው ባላቸው ስራዎች እና በምን መልኩ መደግፍ እንደሚቻል መክረዋል፡፡

በተለይም ደግሞ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባቸውን የጤና አገልግሎቶችን በማዳረስ ዙሪያ ተወያይተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ሄንሪታ ፎርን በትናንትናው እለት በቤጂንግ አግኝተው አነጋግረዋል።

በቆይታቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ ለሚሰራው ስራ ድጋፋቸው እንደማይለያቸው ገልፀዋል።

የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ሄንሪታ ፎር በበኩላቸው በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ድጋፍ ከአዲሱ ለውጥና ስትራቴጂ ጋር አጣጥሞ መስራት እንደሚፈልጉ ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ባሳለፍነው እሁድ ከቻይና ኤግዚም ባንክ ሊቀመንበር ሁ ሺያሊን ጋር መወያየታቸውም ይታወሳል።

በውይይታቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቻይና ኤግዚም ባንክ ለኢትዮጵያ ልማት ወሳኝ ለሆኑ ሜጋ ፕሮጄክቶች ስለሰጠው ብድር ምስጋናችውን አቅርበው የብድር መክፈያው እንዲራዘም እንዲሁም ወለዱ እንዲቀንስ ጠይቀዋል።

የኤግዚም ባንክ ሃላፊዋም በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ያለውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ አድንቀው ከብድሩ ጋር በተያያዘ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሷቸውን ጥያቄዎች በጥንቃቄ ተመልክተው አዎንታዊ ምላሽ እንዲገኝ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።