በሶማሌ ክልል አዲስ የተሾሙት የካቢኔ አባላት የህዝቡን የለውጥ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት መስራት አለባቸው

በቅርቡ  የተሾሙት አዲሶቹ  የሶማሌ ክልል የካቢኔ አባላት የህዝቡን የለውጥ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለባቸው  የፌዴራል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃለፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ አሳሰቡ፡፡

ሚኒስትሩ   አዲስ ከተመረጡት የክልሉ ካቢኔ አባላት ጋር በጅግጂጋ ከተማ  በተወያዩበት ወቅት እንደተናገሩት በክልሉ ተከስቶ የነበረው ችግር ተከትሎ የተፈጠረው የአመራር ክፍተት መልሶ ለማደረጀት መሪ ድርጅቱ እየሰራ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በክልሉ የተዋቀረው አዲሱ  አመራር ለመጀመሪያ ጊዜ በከፍተኛ ጥንቃቄ የተመረጡና  ተገቢውን መንግስታዊ አገልግሎት በማቅረብ ለውጥ እንደሚያመጡ የታመነባቸው ናቸው፡፡

" ህዝብን ማገልገል ትልቅ ክብር ነው፤ የተረከባችሁት ኃላፊነት የህዝቡን መሠረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት በቅንነት መሥራት ይገባል" ብለዋል፡፡

አቶ አህመድ እንዳሉት በቅርቡ በክልሉ ተከስቶ የነበሩ የመልካም አስተዳደርና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በድጋሚ እንዳይኖር  አዲሱ የካቢኔ አባላት ሙስና፣ ጎሰኝነት እና አፍራሽ አስተሳሰቦችን አጠብቆ መታገል ይጠብቅባቸዋል፡፡

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ በበኩላቸው አዲሱ የቢሮ ኃላፊዎች አርብቶ አደሩ ህዝብ በመንግስት ሊፈቱ የሚገቡ በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

" የክልሉ አመራር  ሥልጣን የህዝብ ማገልገያ መሆኑን ተረድታችሁ ህዝቡን ማስቀደም አለባችሁ"ብሏል፡፡

ከአዲሱ አመራር አካላት መካከል  አቶ አደን ፋራህ በሰጡት አስተያየት  የለውጥ እንቅስቃሴውን  ከዳር ለማድረስ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ለመውጣት ጠንክረው  እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

ሌላው የካቢኔ አባል አቶ መሐመድ ፋተሕ በበኩላቸው  በክልሉ በፍትህ ዘርፍና  የልማት ፕሮጄክቶች ላይ የሚፈፀመው ሙስና ለማስቀረት ቅድሚያ በመሥጠት ሥርዓት ለማስያዝ   የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የክልሉን መንግስት የሚመራው የኢትዮጵያ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኢሶዴፓ/ ሊቀመንበር ናቸው፡፡ (ኢዜአ)