ኢትዮጵያ ፣ ኤርትራና ሶማሊያ ያደረጉት ስምምነት የአገራቱን ግንኙነት ወደ ከፍ ያለ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው -ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ርአብይ

የኢትዮጵያ ፣ ኤርትራና ሶማሊያ መሪዎች ያደረጉት ስምምነት የአገራቱን ግንኙነት ወደ ከፍ  ያለ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑን ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ ተናገሩ ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ ከቻይና ኤርትራ ቆይታ በኋላ በዛሬው ዕለት በሠጡት መግለጫ እንደገለጹት የኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ መሪዎች ትናንት በአሥመራ  የደረሱት ስምምነት የሦስቱ አገራት ህዝቦች ለሰላምና ለልማት በጋራ በመሥራት ግንኙነታቸውን እንዲያጠናክሩ የሚያስችል ነው ።   

በኢትዮጵያና ኤርትራን መካከል ቀደም ሲል የተጀመረውን ግንኙነት ተግባራዊ ለማድረግ የምጽዋና አሰብ ወደብን ያሉበትን ደረጃ ትናንት መጎብኘታቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚንስትሩ  በቅርቡም  ወደ ሥራ እንደሚገባ  ተናግረዋል ።

የኤርትራ መንግሥት በአሥመራ ምቹና የተሻለ የኢትዮጵያ ኢምባሲ  እንዲከፈት  ትልቅ ሥራ  መሥራቱን  የገለጹት ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህም  ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ያላቸውን ፍቅርና አክብሮት  የሚገልጽ በመሆኑ ምስጋና እንደሚገባቸው  በመግለጫቸው አስረድተዋል ።

የኢትዮጵያና ኤርትራ በወደብና በአየር ትረንስፖርት ብቻ ሳይሆን በተለያዩ መንገዶች  ግንኙነታቸውን ለማጠናከርን  በአሥመራ  መምከራቸውንም ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ ጠቁመዋል ።