ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ራሳቸውን ማጥፋታቸውን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ

እስካሁን በተደረጉ የምርመራዎች ውጤቶች ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ራሳቸውን አጥፍተዋል ወደሚል መደምደሚያ መድረሱን የፌደራል ፖሊስ ገለጸ፡፡

የፌደራል ፖሊስ ኮሞሽን ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማል እንደገለጹት ግድያውን ለማጣራት ኢንጂነር ስመኘው ከጁባ ወደ አዲስ አበባ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ የማጣራት ስራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

ኢንጂነር ስመኘው ሃምሌ 18/2010 ማታ 4 ሰዓት ላይ ወደ ቤታቸው መግባታቸውንና ታላቅ ልጃቸውን በተደጋጋሚ ትምህርቱን በርትቶ እንዲያጠና ሲነግሩት እንደነበር በመግለጫው ተነስቷል፡፡

በማግስቱ ሃምሌ 19 ጠዋት 12፡ 45 ላይ አንድ ሲኒ ቡና ጠጥተው ከቤት መውጣታቸውን እና ከ 15 ደቂቃዎች በኋላ ህይወታቸው አልፎ የተገኙበት ቦታ ላይ ቆመው እንደነበር ፖሊስ ጠቁሟል፡፡

ከ5 ደቂቃዎች በኋላ ወደ ቢሮ መግባታቸውን እና 1፡ 45 አካባቢ ወደ መጸዳጃ ይመላለሱ እንደነበር የቢሮው ከጥበቃ እና የጽዳት ሰራተኞች እንደተነገረው ፖሊስ አስረድቷል፡፡

ትንሽ ቆይተውም ኢንጂነሩ ካሏቸው ሁለት ሾፌሮች ወደ አንዱ ደውለው ከጠሩት በኋላ የታሸገ ፖስታ እንደሰጡትና ለማን እንደምትሰጥ ደውዬ እንግርሃለሁ እንዳሉት እንዲሁም ሰባት የታሸጉ ፖስታዎችን ለተለያዩ ሰዎች እንደሰጡም ተጠቅሷል፡፡

የፖስታዎቹ ይዘትም በአመዛኙ በስራቸው ላይ ያለባቸውን ጫና የሚገልጹ መሆኑንም የፌደራል ፖሊስ አስረድቷል፡፡

በመጨረሻም 2፡ 30 ላይ የኢንጂነሩ ሞት መረጃ ለፖሊስ እንደደረሰና 2፡40 ላይ ፖሊስ በስፍራው ደርሶ ምናልባት ኢንጂነሩ በህይወት ካሉ ማትረፍ እንዲቻል ፖሊስ የኋላውን መስኮት እንደሰበረውም ተገልጿል፡፡

በወቅቱ በስፍራው ወድቆ የተገኘው ሶፍትና ጓንት የፖሊስ እንደሆነም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

በመኪናቸው ውስጥም ሁለት የታሸጉ ፖስታዎች እና ራሳቸውን ያጠፉበት ሽጉጥ የተገኙ ሲሆን ሽጉጡም በ2 ሺህ ዓም ኢንጂነር ስመኘው ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሞሽን ፈቃድ አውጥተው የታጠቁት መሆኑንም ፖሊስ አረጋግጧል፡፡

ኢንጂነሩ ለምን ለዚህ ውሳኔ እንደደረሱ ፖሊስ በማጣራት ላይ እንደሆነም ኮሚሽነሩ አያይዘው ገልጸዋል፡፡