“ለኢኮኖሚ ዲፕሎማሲያችን ልዩ ትኩረት እንሰጣለን”-ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ

የኢ.ፌዲ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በኢትዮጵያ የስዊዘርላንድ አምባሳደር ዳንዔል ሀልን በትላንትናው እለት (ነሀሴ 30 ቀን 2010 ዓ.ም) በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

ክቡር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ፣ኢትዮጵያና ስዊዘርላንድ ረጀም ዓመታትን ያስቆጠረ ፈርጀ-ብዙ ግንኙነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት  በልማት ትብብር መስክ ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ያላቸው ትብብር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ወደ ላቀ ደረጃ ሊሸጋጋር እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡ 

ፕሮፌሰሩ በኢትየጵያ ያሉትን በርካታና ምቹ የንግድና የኢንቨስትመንት እድሎች እንዲሁም እየተደረጉ ያሉትን የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የስዊዘርላንድ የቢዝነስ ማህበረሰብ ሊጠቀምባቸው ይገባል ብለዋል፡፡

አምባሳደር ዳንኤል ሀል በበኩላቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትብብር ማስፋት ቀዳሚ የሁለትዮሽ አጀንዳ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ እየታዩ ያሉት ለውጦች በስዊዘርላንድ ኩባንያዎች ዘንድ በኢትዮጵያ መዋዕለንዋይ የማፍሰስ ከፍተኛ ፍላጎት ማሳደራቸውንም ገልጸዋል፡፡

በርካታ ኩባንያዎችም ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የቅድመ-ኢንቨስትመንት ጉብኝት ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያና ስዊዘርላንድ መካከል መደበኛ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1924 ዓ.ም ኢትዮጵያ በስዊዘርላንድ የቆንስላ ጽ/ቤቷን መከፍቷን ተከትሎ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ (ምንጭ: የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ )