አዲሱን ዓመት ስንቀበል ጠንካራ አገር ለመፍጠር ያሳያነውን ተነሳሽነት ወደ የላቀ ደረጃ ማሸጋገር ይገባል -ጽህፈት ቤቱ

አዲሱን ዓመት ስንቀበል የተሻለች ጠንካራ አገር ለመፍጠር ያሳየነውን ተነሳሽነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚገባ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ  ።

“በፍቅር እንደመር፤ በይቅርታ እንሻገር“ በሚል መሪ መልዕክት መላው ኢትዮጵያውያን አዲሱን ዓመት ለመቀበል እየተሰናዳ እንደሚገኝም  መግለጫው አመልክቷል ።

እንኳን ለበዓሉ በሰላም አደረሰን! መጪው ዘመንም የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የዕድገት እና የብልጽግና እንዲሆንልን የኢፌዴሪ መንግሥት መልካም ምኞቱን ከወዲሁ ገልጿል ።

የኢትዮጵያውያን ብቻ መሆኑ የተመሰከረለትን የወርሃ ጳጉሜን አምስት ቀናት የሰላም ቀን፣ የፍቅር ቀን፣ የይቅርታ ቀን፣ የመደመር ቀንና የአንድነት ቀን በሚል በነባር ኢትዮጵያውያን እሴቶች ቅኝት ዋዜማውን እያከበሩ  መሆኑን መግለጫው ጠቅሷል ።

ለሦስት አስርት ዓመታት ገደማ ተኳርፈው እና ተራርቀው የነበሩ የአንድ እናት ልጆች፣ ጎራ ለይተው ሲቆራቆሱ የነበሩ የኃይማኖት ተቋማት እና የፖለቲካ ድርጅቶች ከጥላቻ ተላቀው በፍቅር እና በመደመር እሳቤ ተጨባጭ የለውጥ እንቅስቃሴዎች እየታዩ ይገኛሉ ።

በተጨማሪም በደምና በታሪክ ከተሳሰረው የኤርትራ ወንድም ህዝብ ጋር ለዓመታት የዘለቀው የጥላቻ እና የጦርነት አስተሳሰብ ተወግዶ የሁለቱ አገራት ህዝቦች ለጋራ ተጠቃሚነት በጋራ እየሰሩ ባለበት በአሁኑ ወቅት ተወካዮቻቸው የሚታደሙበት በዓል መሆኑም ሌላው መለያው  የዚህ በዓል መለያው መሆኑን መግለጫው አትቷል ።

ኢትዮጵያ የቀደምት ስልጣኔ ምንጭና የነፃነት ጮራ ፈንጣቂ መሆኗን ከሚመሰክሩላት በርካታ ቋሚ ቅርሶች መካከል አንዱ የራሷ ልዩ የዘመን አቆጣጠር ባለቤት በመሆኗ መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው  ከዘመን መቁጠሪያዋ የሚመነጨው የዘመን መለወጫ በዓልም በኢትዮጵያውያን ወግና ባህል መሠረት በየዓመቱ አዲስ ተስፋና ምኞት ይዞ የሚመጣ ታላቅ በዓል ነው ብሏል።

በተለይም ላለፉት ጥቂት ወራት በአገራችን በተጀመረው የለውጥ ነፋስ ታጅቦ፣ በአዲስ የለውጥ ተስፋ እና ብርሃን ተሞልቶ ብቅ ያለው የዘንድሮው በዓል ከቀደሙት በዓላት ጋር ሲነጻጸር ፍጹም የተለየ ክብደት እንዲሰጠው ያደርገዋል።

በተጨማሪም የዘንድሮውን በዓል የጥላቻው ግንብ ፈርሶ በምትኩ የፍቅር ድልድይ እየተገነባ ባለበት ወቅት ላይ የሚከበር መሆኑንም ሌላው  ልዩ የሚያደረገው ጉዳይ መሆኑን መግለጫው  ጠቁሟል ።

ከተጀመረ በጣም አጭር ሊባል በሚችል ጊዜ ውስጥ በመንግሥት የተካሄዱት የለውጥ እርምጃዎች ከአገራችን አልፎ የምንገኝበትን የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና አገራትን ጭምር ተጠቃሚ የሚያደርጉ ውጤቶች የተመዘገቡባቸው ናቸው።

 ከጎረቤት አገራት ጋር እየተካሄደ ባለው የዲፕሎማሲያዊ ጥረት ከንድፈ ሃሳብ ወደ ተግባር እየተሸጋገረ በውጤት እየታጀበ መምጣቱን በጂቡቲ፣ በሶማሌ እና በአሰብ ወደብ አጠቃቀም ዙሪያ የተገኘውን ውጤት እንደ አብነት  መውሰድ እንደሚቻል መግለጫው ጠቁሟል።

በሌላ በኩል፣ ህዝባችን በትልቅ አገራዊ መነቃቃት መንፈስ ውስጥ ሆኖ እያስመዘገባቸው ያሉ ዘርፈ ብዙ ውጤቶች እንደ አገር የሚያኮሩን ሆነው መታየት ጀምረዋል። ነባሮቹን የሰላም ወዳድነት፣ የመፈቃቀር፣ የመረዳዳት እና የመተሳሰብ እሴቶቻችንን እንድናጎለብት በመንግሥት የቀረበውን ጥሪ በሙሉ ልብ በመቀበል ህዝባችን በየአካባቢው እያካሄደው ያለው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ዛሬ ከመቼውም የተሻለች ሰላማዊ አገር እንድትኖረን አስችሏል። “ለእናት አገሬ ስጦታ” በሚል መርህም በእውነተኛ የወገን ፍቅር ላይ የተመሰረተ እና ለአገራችን እጅግ ትልቅ ጠቀሜታ ያላቸውን የበጎ አድራጎት ሥራዎች በማካሄድ ላይ መሆኑን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።

ኢትዮጵያውያን መጪውን አዲስ ዓመት ለመቀበል ሲዘጋጁ ከመቼውም ጊዜ በላቀ መልኩ የፈጠሩትን አገራዊ መግባባት አጠናክረው፣ ሰላሙን ጠብቀው የጋራ ራዕይ እና ተልዕኮ አንግበው ለአገር ግንባታ የጀመሩትን ጥረት ለማጠናከር ቃል በመግባት ሊሆን እንደሚገባው መግለጫው  ጥሪ አቅርቧል።