በድንበር ላይ የነበረው ሰራዊት ወደ ካምፕ እንዲገባና እንዲያገግም ይደረጋል- ዶክተር አብይ

በኢትዮ-ኤርትራ በድንበር ላይ የነበረው ሰራዊት ወደ ካምፕ እንዲገባና እንዲያገግም ይደረጋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ድንበር አካባቢ የነበረው የመከላከያ ሰራዊት ከዛሬ ጀምሮ ወደ ካምፕ በመግባት እንዲያገግም ይደረጋል ብለዋል  የኤፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና ሌሎች የሁለቱ ሀገራት ባለስልጣናት፣ ህዝቦችና ሰራዊቶች ጋር በመሆን ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ድንበር ላይ አዲስ ዓመትን አክብረው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል።

ዶክተር አብይ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በሰጡት መግለጫም፥ ሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ የነበረው የአዲስ ዓመት መቀበያ በዓል አስደሳች እንደነበረ ተናግረዋል።

በቡሬ ድንበር ላይ በተካሄደው የበዓል አከባበር ላይ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሰራዊቶች ተቃቅፈው የጨፈሩበት፤ የሁለቱ ሀገራት ሰንደቅ አላማዎች በክብር የተውለበለቡበት እጅግ በጣም ደስ የሚል ጊዜ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ በዛላምበሳ ድንበር የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች፣ ሰራዊቶች እና መሪዎች በተገኙበት የአዲስ ዓመት በዓል ተከብሯል ያሉ ሲሆን፥ በዚሁ ወቅትም የየብስ ትራንስፖርትን በይፋ የማስጀመር ስራ ተሰርቷል ሲሉም ተናግረዋል።

“የዛሬው የበዓል አከባበር የተካሄደው አዲሱን ዓመት በጋራ እንደምናከብር ቃል መግባታችንን ተከትሎ ነው” ያሉት ዶክተር አብይ፥ ይህም በዛሬው እለት ተሳክቶ ድንበር በማፍረስ በጋራ አዲስ ዓመት ማክበር ችለናል ነው ያሉት።

በዛሬ እለት በነበረው ሁነት ያየነው ነገር እጅግ በጣም የሚያሳዝን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ የሁለቱ ሀገራት ወታደሮች በጣም ሙቀት ባለው ምሽግ ውስጥ ለባንድራ ክብር ሲሉ ለረጂም ጊዜ በመቆየታቸው በጣም ተጎሳቅለዋል ብለዋል።

ሁለቱን ባንዲራ ከጦርነት፣ ከፀብና ከጥላቻ ውጭ በፍቅርና በሰላም እኩል እንዲውለበለቡ ማድረግ እየተቻለ በተቃርኖ የተሰራው ስራ አሳዛኝ ነው፤ ነገር ግን ትምህርት የምንወስድበት ሊሆን ይገባልም ብለዋል።

ከዚህ በመነሳትም ከዚህ በኋላ ከሌሎች ሀገራት ጋርም ይሁን እርስ በእርስ ሰው ለመግደል መበርታት የለብንም፤ ይልቁንም እውቀታችንን እና ጉልበታችንን በመሰብሰብ የሚራቡትን ለማገዝ እና ራስን መለወጥ ላይ መበርታት አለብንም ብለዋል።

በቀጣይ ለመስራት የታሰበው የሰላም፤ የልማትና የዴሞክራሲ ስራ መሰረት እንዲይዝ እና ሰላምን ከፍ አድርገን እንድናስብ በትብብር መስራት ይጠበቃል ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አበይ፥ የኢፌዴሪ መላከያ ሰራዊት ከዛሬ ጀምሮ ድንበር አካባቢ ላይ የነበረውን የጦርነት ስሜት በከፍተኛ ደረጃ ቀንሶ ወደ ካምፕ በመሰብሰብ የሚያገግምበት፣ የሚሰለጥንበት እና ራሱን የሚያበቃበት ሁኔታ ይፈጠራል ብለወዋል።

በኤርትራ በኩልም ተመሳሳይ ስራ እንደሚከናወንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ በኩል ሰራዊቱ ሙሉ በሙሉ ራሱን እስከሚያደራጅ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የአካባቢውን አርሶ አደር በማገዝ ወደ ልማት ስራ ትኩረቱን እንዲያደርግ ይደረጋል ብለዋል።

ከዚያ በኋላ ግን ሙሉ ቁመና ያለው ሰራዊት እንዲሆንና መለዮውን በትክክል የሚያከብር፣ ሰልፍ የሚያሳምር፣ ነገሮችን የመከወን ብቃት ያለው፣ ለመዋጋት በቂ ዝግጅት ያደረገና ከተዋጋ የሚያሸንፍ ሆኖ እንዲደራጅ ማድረግ በቀጣይ የምንሰራው ስራ ይሆናል ሲሉም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አበይ አክለውም የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት እንደ አዲስ እንዲዋቀር ተገርጓል ያሉ ሲሆን፥ በአዲሱ አደረጃጀት መሰረት ያለውን ሀይል ሰብስቦ፣ ራሱን አብቅቶ፣ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለመጠበቅና በልማት ስራዎቿ በመሳተፍ የህዝቦቿ እና የባንዲራዋ አልኝታ መሆኑን የሚያረጋግጥበት ዘመን ከፊታችን ያለ መሆኑ ይሰማኛልም ብለዋል።

በመጨረሻም አዲሱ ዓመት ለመላው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ህዝብ የሰላም፣ የፍቅር፣ የልማት፣ የብልፅግና እና የእግድት እንዲሆን እመኛለሁ ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።