የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር በፈቃዳቸው ሀላፊነታቸውን ለቀቁ

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር በላቸው መኩሪያ በገዛ ፈቃዳቸው ሀላፊነታቸውን መልቀቃቸው ተገለፀ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መኮንን ሀይሉ እንዳረጋገጡት፥ ኮሚሽነር ዶክተር በላቸው መኩሪያ ከመስከረም 1 2011 ዓ.ም ጀምሮ ነው በራሳቸው ፍቃድ ከሀላፊነታቸው ለቀዋል፡፡

ኮሚሽነር ዶክተር በላቸው መኩሪያ በገዛ ፍቃዳቸው ከሀላፊነታቸው የለቀቁበት ምክንያትን ግን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አልገለፁም።

ዶክተር በላቸው መኩሪያ ባሳለፍነው ሚያዚያ ወር 2010 ዓ.ም ነበር የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንን እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የተሾሙት።

ዶክተር በላቸው መኩሪያ የቀድሞ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚነር የነበሩትንና አቶ ፍጹም አረጋ የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት ሀላፊ መሆናቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው መሾማቸውም ይታወሳል።

ከዚያ ቀደም ብሎ በነበሩ ጊዜያት ደግሞ ዶክተር በላቸው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር በመሆንም አገልግለዋል።