በፍታብሄር ጉዳዮች ክርክር ከመገባቱ በፊት ባለ ጉዳዮች በፍላጎቸው ስምምነት የሚያደርጉበት አሰራር ሊተገበር ነው

በፍታብሄር ጉዳዮች ወደ ክርክር ከመገባቱ በፊት ባለ ጉዳዮች በፍላጎቸው ስምምነት የሚያደርጉበት አሰራር በዚህ ዓመት ሊተገበር መሆኑ ተገልጿል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳነት አቶ ዳኜ መላኩ እንደገለጹት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃና ከፍተኛ ደረጃ ፍርድ ቤቶች የሚተገበረው የማስማሚያ ችሎት ባለጉዳዮች ክስ ከመሰማቱ በፊት አስቀድመው ጉዳያቸውን በስምምነት ለመጨረስ የሚያስችል አሰራር ሊተገበር መሆኑን ገልጸዋል።

አሰራሩ በግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ያሉ ተንቀሳቃሽና ተንቀሳቃሽ ያልሆኑ ንብረቶች የፍትሃብሄር ክስ ከመሰማቱ በፊት በባለጉዳዮች ስምምነት በሶስት ወራት ውስጥ እልባት እንዲያገኝ የሚያደርግ መሆኑም ነው የተገለጸው።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በርካታ የፍትህ ማሻሻያ ስራዎች እየሰራ ሲሆን፥ በያዝነው አመት ተግባራዊ ይደረጋል የተባለ የፍታብሄር ጉዳዮች የማስማሚያ ችሎት አሰራር አንዱ መሆኑም ነው የተጠቆመው።

ባለጉዳዮች በመደበኛው የፍርድ ሂደት የመዳኘትና ቀልጣፋ፣ ተደራሽና ፍትሀዊ ውሳኔ የማግኘት መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በአማራጭ በፈቃዳቸው በተመረጠ አስማሚ አማካይነት ጉዳያቸውን በራሳቸው የመፍታት መብት ያላቸው መሆኑን ተከትሎ ነው በአሁን ወቅት ይህ የማስማሚያ ችሎት ተግባር ላይ ይውላል የተባለው።

በአሁኑ ወቅት በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሚመራ የአስማሚነት አገልግሎት በመደበኛነት ለመስጠት የሚያስችል ሥርዓትና መዋቅር የተደራጀ ሲሆን፥ የማስማሚያ ችሎቱ በዚህ አመት ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል።

ባለጉዳዮች ጉዳያቸውን በስምምነት መቋጨት መቻል ከመደበኛው የሙግት አካሄድ ስርዓት አንጻር ሲታይ ችግር ፈቺወች ራሳቸው ባለጉዳዮች በመሆናቸው ጊዜና ወጭ ቆጣቢ መሆኑ ተጠቁሟል።

ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ ረቺና ተረቺ የማይኖርበት ግራቀኙ ተከራካሪ ወገኖች በተቻለ መጠን ፍላጎታቸውን ሊያሳኩ የሚችሉበትን ዕድል ይፈጥራል ተብሏል።

ተስማሚዎች በተለያዩ ሁኔታ መቅረብ ባይችሉ እንኳ ጠበቃ በማቆም በስምምነቱ ላይ መከራከር እንደሚቻልም ተገልጿል።

አሰራር የዜጎችን በአማራጭ ፍትህ የማግኘት መብታቸውን የሚያረጋግጥና ባለጉዳዮች ክስ ከመሰማቱ በፊት አስቀድመው ጉዳዩን በስምምነት ለመጨረስ የሚያስችል ነው ተብሏል።

በፍታብሄር ጉዳይ ላይ በጥብቅና ሙያ የሚያገለግሉት የህግ ባለሙያዎቹ ሙሉጌታ አለሀኝና ዩሃንስ አየሁ የማስማሚያ ችሎት አሰራር ተግባራዊ መሆን ለባለ ጉዳዮች በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት መሆኑን አስረድተዋል።(ኤፍ.ቢ.ሲ)