በኤርትራ በትጥቅ ትግል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የኦነግ አባላት በነገው እለት ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ

በኤርትራ በትጥቅ ትግል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የታጠቁ የኦነግ አባላት ትጥቃቸውን ፈተው በነገው እለት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ ተገልጿል።

በዚሁ ቀን ለግንባሩ አመራሮችም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ደማቅ አቀባበል እንደሚደረግላቸው ነው የተገለጸው።

ከ1300 ስስከ 1500 ያህል አባላት ነገ ጠዋት በዛላንበሳ በኩል የሚገቡ ሲሆን፥ በአዲግራት ህዝብ አቀባበልና የቁርስ ፕሮግራም እንደሚኖራቸው በትግራይ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽ አቅም ግንባታ ሃላፊ የሆኑት አቶ ወልደ ገብረኤል አስገዶም ተናግረዋል።

በተመሳሳይ መልኩ በመቀሌ ከተማም አቀባበልና የምሳ ፕሮግራም እንደሚኖራቸውም አቶ ወልደ ገብሬኤል ገልጸዋል።

በኦሮሚያና አማራ ክልሎች በተለያዩ ከተሞች አቀባበል እንደሚደረግላቸውና ወደ ስልጠና ካንፖች አንደሚገቡም ይጠበቃል።

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ በነገው እለት ከኤርትራ ወደ ኢትዮዽያ የሚገባውን የኦሮሞ ነጻነት ግምባር ኦነግ አባላትና አመራር ቡድንን ለመቀበል ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁ ተነግሯል።

ቡድኑ በቦሌ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደፈርስም ደማቅ አቀባበል የሚደረግለት መሆኑንም ነው የግምባሩ ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ  ገልጸዋል።

በአቀባበል ስነ ሥርአቱ ላይ የሚታደሙት ወጣቶችም ሰላማዊ በሆነ መልክ ድጋፋቸውን እንዲያሳዩም አቶ ቶሌራ አሳስበዋል።

የኦነግ የማእከላዊ ኮሚቴ አመራርን ጨምር ከፍተኛ ቁጥር ያለው አባላት ነው በነገው እለት ሀገራቸው ይገባሉ ተብሎ የሚጠበቀው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ኤርትራ ባደረጉት የመጀመሪያ ጉብኝት ጎን ለጎን አስመራ ከሚገኙ የኦነግ አመራሮች ጋር ወደ ሀገር ቤት በሚመለሱበት ጉዳይ ላይ መወያየታቸው የሚታወስ ነው፡፡

ይህንንም ተከትሎ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁና ከኦሮምያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ጋር በአስመራ ውይይት አካሂደዋል፡፡

ግንባሩም ከሳምንታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ልዑካኑን ልኮ ከመንግስት ጋር በደረሰው ስምምነት መሰረት ውይይት ሲያካሂድ መቆየቱም ይታወቃል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ በርካታ ግለሰቦችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ቤት በመመለስ ላይ ይገኛሉ፡፡ (ኤፍ.ቢ.ሲ)