የኦነግ አመራሮች አዲስ አበባ ገቡ

በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር አመራሮች ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

ለአመራሮቹ ከአዲስ አበባ እና ከኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች የተሰባሰቡ ዜጐች በመስቀል አደባባይ ደማቅ አቀባባል አድርገውላቸዋል፡፡

በአቀባበል ስነ ስርዓቱ ላይ የተናገሩት አቶ ዳውድ ኢብሳ፥ ኦነግ በሀገር ግንባታ ሂደት የበኩሉን ድርሻ ለመጫወት ዝግጁ መሆኑን ነው ያረጋገጡት።

ከመንግስት ተደራድሮ ወደ ሀገር ቤት የገባው ኦነግ ይህ ስምምነት እና በሀገሪቱ የተጀመተረው ለውጥ እንዲሳካ ከመንግስት ጋር በጋራ ይሰራልም ብለዋል።

ይህንን ለውጥ ያመጣው ህዝብ ለውጡ ከዳር እንዲደርስ ራሱ እንዲጠብቀው አሳስበዋል።

በሀገሪቱ ካሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምንም ቅድመ ሁኔታ ሳናስቀምጥም በጋራ እንሰራለን ብለዋል።

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያውያን ተባብረን፤ ሁላችንም ተስማምተን  በጋራ ይህችን ሀገር ወደተሻለ ምእራፍ እናሸጋግራለን ብለዋል።

ተባብረን፤ ተደማምጠን በጋራ የአገር ግንባታ ላይ የምንረባረብበት ምዕራፍ ላይ ደርሰናል ያሉት ምክትል ከንቲባው፥  በዚህ ከቀጠልን ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እናበረክታለን ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ ወጣቶች ለአቀባበል ስነ ስርዓቱ ስኬት ላበረከቱት አስተዋፅኦም ምስጋናን አቅርበዋል።

በተጨማሪም የኦነግ ታጣቂዎች በትግራይ በኩል ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል።

አባላቱ ባለፉባቸው የትግራይ ክልል ከተሞችም በህዝቡ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። (ኤፍቢሲ)