በጅማ ከተማ የሚካሄደው 9ኛው የኦህዴድ ድርጅታዊ ጉባኤ ዝግጅት ተጠናቋል

ከነገ በስትያ በጅማ ከተማ የሚካሄደው 9ኛው የኦህዴድ ድርጅታዊ ጉባኤ ዝግጅት መጠናቀቁን አስታወቀ ። 

የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት የገጠር ፖለቲካ ዘርፍ አደረጃጀት ኃላፊና የጉባኤው ቃል አቀባይ አቶ አዲሱ አረጋ ትናንት በጅማ ከተማ በሠጡት መግለጫ እንደተናገሩት ጉባኤው ‘‘የላቀ ሃሳብ ለተሻለ ድል’’ በሚል መሪ ቃል ይካሄዳል።    

በጉባኤው ላይ በድምጽ የሚሳተፉ 1ሺህ66፣ በታዛቢነት የሚሳተፉ 250 ሰዎች ጂማ ከተማ ተጠቃለው መግባታቸውንም አመላክተዋል።

በጉባኤው ታሪካዊ ውሳኔዎች የሚተላለፉ መሆኑን ያመላከቱቱት ሃላፊው በዚሁ ጉባኤም ያለፉት ሶስት ዓመታት የውስጥ ድርጅት አፈጻጸም ይገመገማል፤ የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽን ሪፖርትም ቀርቦ ይውውይት የሚካሄድበት መሆኑን አስረድተዋል።

በጉባኤው ቆይታ የድርጅቱን ስያሜ፣ አርማ እና መዝሙር ለመቀየር የሚያስችል ረቂቅ ቀርቦም ውይይት እንደሚካሄድበት ነው አቶ አዲሱ የተናገሩት።

የፊታችን ማክሰኞ ከሰዓት በኋላም 6ሺህ ታዳሚዎችና የኦህዴድ ኢህአዴግ ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አህመድ በተገኙበት ደማቅ የመክፈቻ ስነ ስርዓት እንደሚደረግም ነው አቶ አዲሱ የገለጹት።(ኤፍ.ቢ.ሲ)