መንግሥት የህዝቡን ደህንነትና ሰላም ለማስጠበቅ እርምጃ እንደሚወስድ የፌደራል ፖሊስ አስታወቀ

መንግሥት የህዝቡን ደህንነት እና ሰላም ለመጠበቅ አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ እንደሚወስድ የፌደራል ፖሊስ  አስታወቀ ።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከሚሽነር ጀነራል ዘይኑ ጀማል ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተከሰቱ ጉዳዮችን  በተመለከተ በዛሬው ዕለት በሠጡት መግለጫ የመንግስት ትዕግስት ገደብ እንዳለው በመግለፅ ጉልበተኞችን እንደማይታገስ ተናግረዋል ።

ሰሞኑን በአዲስ አበባ እየተፈጠሩ  ያሉት ሁከቶች በሁለት የፖለቲካ ድርጅቶች ስም የተቀነባበሩ ስለ መሆናቸውን ኮሚሽነር ጀነራሉ ጠቁመዋል።

ባለፉት ሦስት ቀናት በቡራዩና አካባቢው በተፈጠሩ ብጥብጦች  ብዛት ያላቸው ወንጀለኞች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና  በተለያዩ ቦታዎች የተዘረፉ  ንብረቶች  ታድነው ካሉበት  የማሰባሰብ ስራ መሰራቱንም ነው ያስታወቁት።

በአጠቃላይም በቡራዩ ሁከት  ውስጥ  እጃቸውን  አስገብተዋል  የተባሉ  ከ300 አስከ 400 የሚደርሱ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን በአዲስ አበባ ደግሞ ከ300 በላይ ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ገንዘብ ተከፍሏቸው ብሄርን ከብሄር ለማጋጨት ፣ ብሄርን መሰረት ያደረጉ ስድብ አዘል መልክዕቶችን በማስተላለፍና በማሠራጨት ግለሰቦች የተጠረጠሩ ግለሰቦች ተይዘዋል ብለዋል  ።

ይህ ድርጊት በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባና በአርባ ምንጭ መታየቱን ጠቅሰዋል።

በቡራዩና አካባቢው የተፈፀመውን ግድያ ለማውገዝ በርካታ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላማዊ ነዋሪ

መውጣቱን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ  የተወሰኑ ቡድኖች ግን አዝሚሚያቸው ሌላ እንደነበር ገልጸዋል ።

ሰለፍ ከወጡ መካከልም የተወሰኑ ግለሰቦች  ቦምብ ይዘው እንደነበሩና  በህብረተሰቡ ትብብር መያዛቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በፒያሳና በመርካቶ ለዝርፊያ የሚቃጡ ግለሰቦች እንደነበሩ ነው የጠቀሱት።

የተወሰኑት የጸጥታ ኃይሎችን ደግሞ ጠመንጃ ለመንጠቅ ሙከራ ያደረጉ ሲሆን በዚህም ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ግብግብ ገጥመዋው እንደነበርና በዚህም ምክንያት የአምስት ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፥ ቁጥራቸው ያልተወቁ ሰዎች መቁሰላቸውን ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በአዲስ አበባ  የተፈጠረው  ሁከት  የተጀመረውን ለውጥ እንዳይሳካ ታስቦበት የተፈጸመ ስለመሆኑን  ኮሚሽነሩ  ተናግረዋል ።