የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል መንግስት በቡራዩና አከባቢዋ በደረሰው የህይወትና ንብረት ውድመት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማው ገለጸ

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል መንግስት በቡራዩና አካባቢዋ በተፈጠረው ግጭት በህይወትና በንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማው ገለፀ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ በቡራዩና አከባቢዋ የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ በደረሰው ጉዳት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማቸው ነው የተናገሩት።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከተፈናቀሉት ውስጥ 300 አባወራዎች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ጠቅሰው፥ ቀሪዎቹንም ወደ ቀያቸው ለመመለስና መልሶ ለመቋቋም የክልሉ መንግስት ሙሉ ኃላፊነት ወስዶ ይሰራልም ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በግጭቱ እጃቸው አለበት የተባሉ ከ200 በላይ ተጠርጣሪዎችና የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችም በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውቀዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ግጭቱን ወደተለያዩ አከባቢዎች ለማዛመት መሞከሩንም ጠቅሰው፥ ህብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ባደረገው ትብብር በቁጥጥር ስር መዋሉንም አንስተዋል።

ይህንን ግጭት ሌላ መልክ በመሥጠት ወደ አሰላ አከባቢ ለማስፋፈት መሞከሩንም ጠቅሰው፥ ህብረተሰቡ በሰከነና ማስተዋል በታከለበት ሁኔታ ሊንቀሳቀስ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ከፌደራልና ከኦሮሚያ ፖሊስ የተውጣጣ ግብረ ኃይል ተዋቅሮ ያሉትን ሁኔታዎች ለማርገብና እንዲሁም ወደፊት ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ለመከላከል እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎችና አክቲቪስቶች የሚያስተላልፉት መልዕክት ህዝቦችን የሚያቀራርብ ወደ አንድነት እንዲመጣ የሚያደረግ እንጂ የሚያለያይ ሊሆን እንደማይገባም አቶ ለማ አሳስበዋል።

መንግስት ነገሮችን በትዕግስት የሚያልፍበት ሁኔታ እንደማይኖርም ርዕሰ መስተዳድሩ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።(ምንጭ: የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን)