የአዲስ አበባ የቧንቧ ውኃ አልተበከለም

በአዲስ አበባ ከተማ “የቧንቧ ውሃ ተበክሏል እንዳትጠጡ” በሚል በማህበራዊ ድረ ገጾች የሚናፈሰው መረጃ ሀሰት መሆኑንና የከተማዋ ውሃ ንጽህና የተጠበቀ እነደሆነ የአዲስ አበባ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን የስራ ሂደት ኃላፊ አቶ እስጢፋኖስ ብስራት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ የከተማዋ የቧንቧ ውሃ ተበክሏል የሚለው መረጃ ከእውነት የራቀ ነው። የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባለሙያዎች ከግድቦቹና ከየማሳራጫ ቦታዎች ናሙና በመውሰድ በላቦራቶሪ ፍተሻ እያደረጉ ናቸው። እስከሁን ድረስም በተደረጉ ፍተሻዎች ለከተማዋ የሚቀርበው ውኃ ደህንነት መቶ በመቶ አስተማማኝና ንጽህናው የተጠበቀ መሆኑ ተረጋግጧል።

በማህበራዊ ሚዲያ እየተወራ ያለው ጉዳይም የተለመደና በከተማዋ የሆነ ውጥረት ሲነሳ አብሮ የሚነዛ የፈጠራ ወሬ ነው ያሉት አቶ እስጢፋኖስ፤ ተጠቃሚው ህብረተሰብ ያለምንም ስጋት የቧንቧ ውኃን መጠቀም እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ማብራሪያም፤ እስካሁን ከውሃ መበከል ጋር በተያያዘ ለባለስልጣኑ ከህክምና ተቋማትም ይሁን ከሌሎች አካላት የቀረበለት ሪፖርትም ሆነ ጥቆማ የለም።